ምሩቃን ያገኙትን እውቀትና ከህሎት ተጠቅመው ስራ ፈጣሪ መሆን ይገባቸዋል - ኢዜአ አማርኛ
ምሩቃን ያገኙትን እውቀትና ከህሎት ተጠቅመው ስራ ፈጣሪ መሆን ይገባቸዋል
ደሴ /ደብረ ብርሃን፣ ሐምሌ 11/2018(ኢዜአ)፡- ምሩቃን በኮሌጅ ቆይታቸው ያገኙትን እውቀትና ከህሎት ተጠቅመው ሥራ ፈጣሪና የልማት አርበኛ ሊሆኑ እንደሚገባ ተጠቆመ።
በደሴ ከተማ የሚገኘው የወይዘሮ ስሂን ፖሊ ቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ኮሌጅ በተለያየ ፕሮግራሞች ያሰለጠናቸውን 422 ተማሪዎች ዛሬ አስመርቋል።
የደብረ ብርሃን ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በበኩሉ ለ29ኛ ጊዜ በተለያዩ የሙያ መስኮች ያሰለጠናቸውን 241 የጤና ባለሙያዎችን ዛሬ በዲፕሎማ መርሃ ግብር አስመርቋል።
የደሴ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ሽመልስ ጌታቸው በምረቃው ላይ እንደገለጹት፣ ተመራቂዎች ስራ ጠባቂ ሳይሆኑ የራሳቸውን ሥራ በመፍጠር ሌሎችን ተጠቃሚ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።
በተጨማሪም ወደ ስራ ከመሰማራት ጎን ለጎን ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ የሰላም አምባሳደርነት ተልእኮን አንግበው ለሀገር ሰላምና ለህዝብ አንድነት መስራት ይጠበቅባቸዋል ሲሉ አሳስበዋል።
የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ኮሌጁ ዲን አቶ ሰለሞን ይመር በበኩላቸው፣ ኮሌጁ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ ብቁና ተወዳዳሪ የሰለጠነ የሰው ኃይል እያፈራ ይገኛል ብለዋል።
በተለይም አዲሱ የትምህርት ፖሊሲ በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪነትን ለመፍጠር የሚያስችል በመሆኑ ተማሪዎቹ በደረጃ አራትና አምስት በ12 የትምህርት መስክ አሰልጥኖ ማስመረቁን ነው የገለጹት
ምሩቃኑ በኮሌጅ ቆይታቸው ያገኙትን እውቀትና ክህሎት ተጠቅመው የራሳቸውን ስራ በመፍጠር በአገራችን እድገት ላይ ተደማሪ ሀብት መፍጠር ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
ከተመራቂዎች መካከል ጀሚላ ሰይድ እና ረድኤት ይመር በበኩላቸው ፣በትምህርት ቆይታ ያገኙትን እውቀትና ልምድ ተጠቅመው ስራ ፈጣሪ ለመሆን እንደሚሰሩ ነው የገለጹት።
በሌላ በኩል የደብረ ብርሃን ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ለ29ኛ ጊዜ በተለያዩ የሙያ መስኮች ያሰለጠናቸውን 241 የጤና ባለሙያዎች ዛሬ አስመርቋል።
የሰሜን ሸዋ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ ፀዳለ ሰሙንጉስ በምረቃው ላይ እንደገለጹት ፤ ዘመናዊ የጤና ስርዓትን በመገንባት ፣ የአገልግሎት አሰጣጡንና ጥራቱን ለማሻሻል ትኩረት ሰጥቶ እየተሰራ ነው።
በዚህም የጤና ተቋማትን ዲጅታላይዝ፣ ጽዱና ውብ በማድረግ በሽታን ቀድሞ በመከላከል፣ አክሞ በማዳንና ተደራሽነት ላይ በማተኮር ለህብረተሰቡ ጥራት ያለው አገልግሎት እየተሰጠ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ በቀለ ገብሬ በበኩላቸው፤ ተመራቂዎች ሙያዊ ስነ ምግባርና ህዝባዊነትን በመላበስ በተለይ የእናቶችና የህፃናትን ሞት ለመቀነስ መስራት እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል።
በሚመደቡበት አካባቢዎችም የማህበረሰቡን ባህል፣ ወግና እሴት መጠበቅን ጨምሮ የታካሚዎችን ሚስጥር በመጠበቅ በቅንነት እንዲያገለግሉ ነው መልእክታቸውን ያስተላለፉት።
የደብረ ብርሃን ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዲን አቶ ማሙየ መንገሻ በበኩላቸው፤ኮሌጁ ዘመኑን የዋጀ እውቀትና ክህሎት በማስጨበጥ ብቁና ተወዳዳሪ የጤና ባለሙያዎችን በማፍራት ላይ ይገኛል ብለዋል።
ተመራቂዎቹ በጤና ኤክስቴሽን፣ በነርስ ፣ በላብራቶሪ ቴክኒሻል፣ በድንገተኛ ህክምና እና በፋርማሲ የሙያ መስኮች መሰልጠናቸውን ነው የገለጹት።
ከተመራቂዎች ውስጥ በላብራቶሪ ትምህርት መስክ 3.95 በማምጣት በማእረግ የተመረቀችው አስናቁ ዝይን የተለያዩ ችግሮችን ተቋቁማ ውጤት ማስመዝገቧን ነው የገለፀችው።
በኮሌጅ ቆይታዋ ያገኘችውን በተግባር የተደገፈ እውቀትና ክህሎት በመጠቀም ህብረተሰቡን በፍቅርና በቅንነት ለማገልገል መዘጋጀቷን ገልጻለች።