ህብረተሰቡን ያሳተፈ የትምህርት ጥራትን የማረጋገጥ ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል - ኢዜአ አማርኛ
ህብረተሰቡን ያሳተፈ የትምህርት ጥራትን የማረጋገጥ ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል
ዲላ፤ ሐምሌ 11/2018 (ኢዜአ)፡- በጌዴኦ ዞን በህብረተሰቡ ተሳትፎ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የተጀመሩ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የዞኑ አስተዳደር አስታወቀ፡፡
በዞኑ “ለትምህርት ያለ ስስት” በሚል መሪ ሀሳብ የትምህርት የንቅናቄ መድረክ ዛሬ በዲላ ከተማ ተካሂዷል።
የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ዝናቡ ወልዴ (ዶ/ር) በወቅቱ እንዳሉት ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ የትምህርት መሰረተ ልማትን ማሟላት መሰረታዊ ጉዳይ ነው።
የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ በህብረተሰቡ ተሳትፎ የተከናወኑ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ የማሻሻልና ግብዓት የማሟላት ተግባራት ውጤታማ መሆናቸውን እንስተዋል።
በዞኑ በቀጣይም ሃብት በመመደብ የትምህርት ውጤታማነትን ለማጠናከር በትኩረት እንደሚሰራ አመላክተዋል።
እድሜው ለትምህርት የደረሰን ወደ ትምህርት ቤት ለማምጣትና ተማሪዎች በግብዓት ችግር ከትምህርት ገበታቸው እንዳይስተጓጎሉ የሚደረግ የተቀናጀ ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመላክተዋል።
ንቅናቄው እውቀትን፣ ገንዘብንና ጉልበትን ያለ ስስት ለትምህርት ልማት በማዋል የትምህርት ጥራትና ተገቢነትን ማረጋገጥ ዓላማ ያደረገ መሆኑን ያነሱት ደግሞ የጌዴኦ ዞን ትምህርት መምሪያ ሃላፊ አቶ ዘማች ክፍሌ ናቸው።
በተጠናቀቀው የትምህርት ዘመን ህብረተሰቡን በማስተባበር ከ36 ሺህ ለሚልቁ ተማሪዎች የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ መደረጉን አንስተዋል።
አንዲሁም ምቹ የመማሪያ አካባቢ በመፍጠር ረገድ ከ141 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የትምህርት ቤቶች ደረጃ ማሻሻል ስራ መከናወኑን ጠቅሰዋል።
በቀጣይ የትምህርት ዘመንም የህብረተሰቡንና የአጋር አካላትን ተሳትፎ በማጠናከር የትምህርት ጥራትና ተገቢነትን ለማረጋገጥ በትኩረት እንደሚሰራ አመላክተዋል።
ለዚህም መምህራን፣ ተማሪዎችና የትምህርት አመራሩ ቅንጅት መጠናከር እንዳለበት አንስተው በተለይ የትምህርት መሰረተ ልማትን በማስፋት ረገድ የጋራ ጥረት ማጠናከር ይጠይቃል ብለዋል።
የጌዴኦ ዞን መምህራን ማህበር ሰብሳቢ መምህርት ገነት ኡልፋታ በበኩላቸው የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የትምህርት ቤቶች መሰረተ ልማት ማስፋፋት፣ የመማሪያ ግብዓቶችን ማሟላትና የመምህራን አቅም ግንባታ የላቀ ድርሻ እንዳላቸው አንስተዋል።
በቀጣይ የትምህርት ዘመን የተሻለ የትምህርት አሰጣጥና የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል በበለጠ በቅንጅት እንደሚሰራ አመላክተዋል።