በአዲስ አበባ ከተማ የተከናወነው የኮሪደር ልማት ከተማዋን ወደ ቱሪዝም መዳረሻነት አሸጋግሯል - ኢዜአ አማርኛ
በአዲስ አበባ ከተማ የተከናወነው የኮሪደር ልማት ከተማዋን ወደ ቱሪዝም መዳረሻነት አሸጋግሯል
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 11/2018(ኢዜአ)፦በአዲስ አበባ ከተማ የተከናወነው የኮሪደር ልማት ከተማዋን ከቱሪዝም መሸጋገሪያነት ወደ ቱሪዝም መዳረሻነት እንዳሸጋገራት የአዲስ አበባ ቱሪዝም ኮሚሽን ኮሚሽነር ሁንዴ ከበደ ገለጹ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የ2018 በጀት ዓመት ማጠቃለያ የሥራ አፈጻጸም ግምገማ በማካሄድ ላይ ይገኛል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በወቅቱ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር፤ በበጀት ዓመቱ ለመፈጸም የተቀመጡ ግቦች እንዲሁም የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ አፈጻጸም እንደሚገመገም ገልጸዋል።
የአዲስ አበባ ቱሪዝም ኮሚሽን ኮሚሽነር ሁንዴ ከበደ እንደገለጹት፤ ባለፉት የለውጥ ዓመታት ለቱሪዝም ዘርፉ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት እየተሠራ ይገኛል።
በዚህም የዘርፉን ማነቆዎች በመፍታት እንዲሁም በፖሊሲ ጭምር በመደገፍ ዋና የኢኮኖሚ ምሰሶ ማድረግ መቻሉን ጠቁመዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ የተከናወነው የኮሪደር ልማት ከተማዋን ከቱሪዝም መሸጋገሪያነት ወደ ቱሪዝም መዳረሻነት ማደጉን ጠቁመዋል።
በኮሪደር ልማቱ እየተገነቡ ያሉ መሠረተ ልማቶች የዘርፉን ተወዳዳሪነት ከፍ እያደረጉ መምጣታቸውንም ጠቁመዋል።
ይህም በዘርፉ የተከናወነው ሥራ ውጤታማ መሆኑን የሚያሳይ መሆኑን ጠቅሰው፤ የኮንፈረንስ ቱሪዝም ሌላኛው ትሩፋት መሆኑን ጠቁመዋል።
በአዲስ አበባ በዘንድሮው በጀት ዓመት 221 ስብሰባዎች መካሄዳቸውን ጠቁመው፤ ባለፈው ዓመት ከ150 በላይ ዓለም አቀፍና አህጉር አቀፍ ስብሰባዎች ተካሂደው እንደነበር አስታውሰዋል።
በአጠቃላይ በቱሪዝም ኢንዱስትሪው በመሠረተ ልማትና በአገልግሎት የተከናወኑ ሥራዎች ትልቅ ለውጥ ያመጡ መሆናቸውን ጠቁመዋል።