ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ በስኬት እየተካሄደ ነው - ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 11/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ በስኬት እየተካሄደ መሆኑን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ገለጹ፡፡

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ሐምሌ 08 ቀን 2018 ዓ.ም መጀመሩ የሚታወቅ ሲሆን ከ4 ሺህ በላይ ተመካካሪዎች እየተሳተፉበት ይገኛሉ፡፡

በአዲስ አበባ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል በመካሄድ ላይ የሚገኘውን የምክክር ሂደት በተመለከተ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

በመግለጫቸውም ሐምሌ 08 በተካሄደው የመክፈቻ መርሐ ግብር ከወረዳ እስከ ፌዴራል ያሉ የህብረተሰብ ክፍሎች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ዲፕሎማቶችና በውጭ ሀገር የሚኖሩ ዳያስፖራ አባላትን ጨምሮ በርካታ ታዳሚዎች በተገኙበት በይፋ መጀመሩን አስታውሰዋል፡፡

ተሳታፊዎች በስምንቱ ሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ በዝርዝር እንዲወያዩና በስምንት ቡድኖች የማደራጀትና የግንዛቤ ፈጠራ ስራዎች መከናወናቸውን ጠቁመዋል፡፡

የሀገራዊ መግባባት ሂደት በምክክር የሚሳካ መሆኑን ጠቅሰው፣ በሂደቱም ከስምንቱ ቡድኖች የሚመነጩ ሀሳቦች እንዴት ወደ አንድ አጀንዳ እንደሚመጡ በዝርዝር ማብራሪያ መሰጠቱን ገልጸዋል፡፡

ተሳታፊዎች ለምክክሩ የሚያስፈልጓቸውን ስልጠናዎች እንዲያገኙ የተደረገ ሲሆን፣ የኮሚሽኑ ባለሙያዎችም ለሂደቱ ስኬታማነት አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረጉ ይገኛሉ ነው ያሉት፡፡

በምክክር ጉባኤው ከዚህ ቀደም ጥሪ ተደርጎላቸው ሳይሳተፉ የቆዩ አዳዲስ የፖለቲካ ፓርቲዎች አሁን ላይ በሂደቱ ለመሳተፍ ፍላጎት በማሳየታቸው ጉባኤውን እንዲቀላቀሉ መደረጉን ጠቅሰዋል፡፡

እስካሁን በሂደቱ ያልተሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ታጣቂዎች ወደ ምክክሩ እንዲመጡም ዋና ኮሚሽነሩ በድጋሚ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡

ከሚቀጥለው ሰኞ ጀምሮ ሙሉ በሙሉ ከጠዋት እስከ ማታ ስራዎቻችንን በየቦታው ተከፋፍለን የምንሰራበት ጊዜ መቶ በመቶ ይጀምራል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነሮችና ኤክስፐርቶቻቸው ለሂደቱ መሳለጥ አስፈላጊውን ሁሉ እንደሚያደርጉም ጠቅሰዋል፡፡

መገናኛ ብዙሃን የኮሚሽኑን ስራ ለህዝብ በማድረስ እያደረጉት ላለው አስተዋጽኦ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም