ቀጥታ፡

ህገ-ወጡ የህወሓት ቡድን በትግራይ ክልል እየፈጸመ ያለውን አስገዳጅ ወታደራዊ ምልመላ በአስቸኳይ ሊያቆም ይገባል

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 11/2018(ኢዜአ)፦ ህገ-ወጡ የህወሓት ቡድን በትግራይ ክልል እያደረሰ ያለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰትና አስገዳጅ ወታደራዊ ምልመላ በአስቸኳይ ሊያቆም እንደሚገባ የትግራይ ተወላጆች ገለጹ።

በትግራይ የሰላምና ለውጥ ምክር ቤት አስተባባሪነት "አፈሳ ይቁም፥ ሰላም ይስፈን" በሚል መሪ ሀሳብ የተዘጋጀ ታላቅ ሰላማዊ ሰልፍ በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ ተካሂዷል።

ሰልፉ በሕገ-ወጡ የህወሓት ቡድን በትግራይ ክልል ሕዝብ ላይ እየተፈጸመ ያለውን አፈና፣ ጭቆና እና የግዳጅ ድርጊቶች ለማውገዝ የተዘጋጀ መሆኑ ታውቋል።

የሰልፉ ተሳታፊዎች በትግራይ ክልል አስተማማኝ ሰላም እንዲሰፍንና ሕዝቡ የልማት ተቋዳሽ እንዲሆን ቡድኑ ህገ ወጥ ተግባራቱን ሊያቆም ይገባል ብለዋል፡፡

ቡድኑ የትግራይን ወጣት ለእልቂትና ለስደት እየዳረገ መሆኑን ጠቅሰው፤ የቡድኑ መሪዎች ልጆቻቸውን በውጭ ሀገራት አስቀምጠው የትግራይ ወጣቶችን ግን በማፈስ እየሸጡ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አቶ ጌታሁን አያሌው በሰጡት አስተያየት፤ ህገ-ወጡ የህወሓት ቡድን እየፈጸመ ያለው እኩይ ድርጊት የቡድኑ አረመኔያዊነት የሚያሳይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ወጣት ዮናስ ደስታ በበኩላቸው፤ በትግራይ ክልል ወጣቶች በህገ ወጥ ቡድኑ እየታፈሱና እየተሸጡ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ቡድኑ ይህን እኩይ ተግባሩን ሊያቆም ይገባል ብለዋል፡፡

የክልሉን ህዝብ በተለይም የወጣቱን ሕይወት መታደግ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ መሆኑን አስተያየት ሰጪው ተናግረዋል።

ወይዘሮ ዘላለም አዲስ በበኩላቸው፣ ህገ ወጥ ቡድኑ ልጆችን ከእናቶች እቅፍ እየነጠቀ በመሆኑ ይህን ማስቆም ይገባል ብለዋል፡፡

አሁን ላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚፈልገው ሰላምን፣ ሰርቶ ማደግንና ልማትን እንጂ ጦርነትን እንዳልሆነ የተናገሩት ደግሞ ወይዘሮ ጀሚላ ኢብራሂም ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም