ሁሉንም አካታች ያደረገው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ በጥሩ ሁኔታ እየተካሄደ ይገኛል - ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ - ኢዜአ አማርኛ
ሁሉንም አካታች ያደረገው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ በጥሩ ሁኔታ እየተካሄደ ይገኛል - ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 11/2018(ኢዜአ)፦ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል አሳታፊ ያደረገው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ በጥሩ ሁኔታ በመከናወን ላይ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ አስታወቁ።
ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ፣ እየተከናወነ የሚገኘውን የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ሂደት አስመልክቶ ዛሬ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥተዋል።
በጉባኤው ላይ የተሳተፉ አራት ሺህ ልዑካን በቀረቡት ስምንት አጀንዳዎች ዙሪያ እየተወያዩ እንደሚገኙም አመልክተዋል።
ምክክሩ ሁሉንም አካታች በሆነ መልኩ እየተከናወነ መሆኑን የጠቀሱት ዋና ኮሚሽነሩ፣ በተሳታፊዎቹ መካከልም ከሀገር ውስጥ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች እንዲሁም በውጭ ሀገር የሚኖሩ የዳያስፖራ አባላት እንደሚገኙበት ተናግረዋል።
ጉባኤው በጥሩ ሁኔታ እየተካሄደ እንደሚገኝና በቀጣይ ቀናትም በአጀንዳዎቹ ዙሪያ ጠለቅ ያሉ ውይይቶች እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።
የምክክር ጉባኤው ከተጀመረ በኋላ፣ ከመጀመሪያዎቹ ተሳታፊዎች ውጪ የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ሌሎች የማህበረሰብ ክፍሎች ለመሳተፍ ያቀረቡትን ጥያቄ ኮሚሽኑ በመቀበል በውይይቱ ላይ እንዲካተቱ ማድረጉንም አስታውቀዋል።
በምክክር ጉባኤው መሳተፍ የሚፈልጉ አካላት አሁንም በሂደቱ ላይ መሳተፍ የሚችሉ መሆኑን በመጥቀስ ጥሪ አቅርበዋል።