ቀጥታ፡

የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉን በማስፋፋት ለሀገር እድገትና ማንሰራራት መሰረት እንዲሆን ይሰራል- ርእሰ መስተዳድር እንደሻው ጣሰው (ዶ/ር)

ሆሳእና፤ ሐምሌ11/2018 (ኢዜአ )፡- በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉን በማስፋፋት ለሀገር እድገትና ማንሰራራት መሰረት እንዲሆን እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) ገለፁ።

ርዕሰ መስተዳድሩ በሆሳዕና ከተማ በግማሽ ቢሊየን ብር ወጪየተገነባውን የዓለም የከረጢት ፋብሪካን መርቀው ስራ አስጀምረዋል።


 

ርዕሰ መስተዳድሩ በወቅቱ እንደገለጹት በክልሉ የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉን በማስፋፋት ለሀገር እድገትና ማንሰራራት መሰረት እንዲሆን ጥረት እየተደረገ ነው።

በዚህም አዳዲስ ኢንዱስትሪዎችን የማቋቋምና ዘርፉን የማበረታታት ስራ ትኩረት የተሰጠው መሆኑን ተናግረዋል ።

በዘርፉ ተኪ ምርትን በማምረት የውጪ ምንዛሬ ከማስገኘት  ባለፈ  የስራ እድል እንዲፈጠር እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል ።

በክልሉ ምቹ የኢንቨስትመንት ከባቢን በመፍጠር የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው በዘርፉ የሚሰማሩ ባለሀብቶችን በመደገፍ ተጨባጭ ውጤት ለማስመዝገብ ትኩረት መሰጠቱን ተናግረዋል።

ዘርፉን በመደገፍ የከተሞችን እድገትና የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ምቹ ሁኔታ የመፍጠር ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።


 

የሀድያ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የገቢዎች መምሪያ ሀላፊ አቶ ደነቀ ጊቻሞ በበኩላቸው የመደመር መንግስት ለግል ዘርፉ በሰጠው ትኩረት በርካታ አምራች ኢንደስትሪዎች ወደ ስራ እየገቡ ነው ብለዋል።

በዚህም የዘርፉ ተኪ ምርቶችን የማምረት፣ የውጪ ምንዛሬን የማስገኘትና የስራ እድል የመፍጠር አቅም መጎልበቱን ተናግረዋል።

የፋብሪካው ባለቤት አቶ ፀደቀ ጌታቸው በበኩላቸው  ፋብሪካው በግማሽ ቢሊየን ብር ወጪ መገንባቱን ተናግረዋል ።


 

ፋብሪካው ከ350 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ እድል መፍጠር መቻሉንም አንስተዋል ።

በፋብሪካው በተፈጠረለት የስራ እድል በሚያገኘው ገቢ ራሱንና ቤተሰቡን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ የገለጸው ደግሞ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋም የተመረቀው ወጣት ዮናስ መለሰ ነዉ።

በምረቃ ስነ ስርአቱ  ላይ የክልል፣ የሀድያ ዞንና የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር የስራ ኃላፊዎች እና የአካባቢው ነዋሪዎች ተገኝተዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም