ጨፌው በክልሉ በተከናወኑ የሰላምና የልማት ሥራዎች ላይ በጥልቀት በመምከር የቀጣይ የሥራ አቅጣጫዎችን ያስቀምጣል - ኢዜአ አማርኛ
ጨፌው በክልሉ በተከናወኑ የሰላምና የልማት ሥራዎች ላይ በጥልቀት በመምከር የቀጣይ የሥራ አቅጣጫዎችን ያስቀምጣል
አዳማ፤ ሐምሌ 11/2018(ኢዜአ)፦ ጨፌው በኦሮሚያ ክልል በተከናወኑ የሰላምና የልማት ሥራዎች ላይ በጥልቀት በመምከር ቀጣይ አቅጣጫዎችን ያስቀምጣል ሲሉ የጨፌ ኦሮሚያ አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ሰዓዳ አብዱራህማን ገለጹ።
የጨፌ ኦሮሚያ 6ኛ የሥራ ዘመን 5ኛ ዓመት 11ኛ መደበኛ ጉባኤ ነገ በአዳማ ገልመ ጨፌ ይጀመራል።
የጨፌ ኦሮሚያ አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ሰዓዳ አብዱራህማን ጉባኤውን በማስመልከት በሰጡት መግለጫ ጨፌው በቆይታው የክልሉ መንግሥት የ2018 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም፣ የ2019 ዕቅድና የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ በጥልቀት ይመክራል ብለዋል።
በተጨማሪም የጠቅላይ ፍርድ ቤትና የጠቅላይ ኦዲት ሪፖርቶችን መርምሮ፣ የ2019 በጀት ዓመት የማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ማስፈጸሚያ እንዲሁም ተጨማሪ በጀትን ያጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል።
ጨፌው የዳኞች ሹመትንም ያጸድቃል ያሉት አፈ ጉባኤዋ፤ ጉባኤው በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ እና በሀገራዊ ምክክር ወቅት መካሄዱ ልዩ እንደሚያደርገው ገልጸዋል።
ጨፌው በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በክልሉ በተከናወኑ የማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ እንዲሁም የሰላምና ጸጥታ ሥራዎችና በተገኙ ውጤቶች ላይ በጥልቀት እንደሚመክርም አስታውቀዋል።
የፍትሕ አገልግሎት አሰጣጥ፣ በጠቅላይ ኦዲት የተሠሩ ሥራዎችና የተመዘገቡ ውጤቶች በጥልቀት ከሚመክርባቸው አጀንዳዎች መካከል እንደሚገኙበት ጠቁመዋል።
የ2019 በጀት ዓመት የማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ማስፈጸሚያ የሚውል በጀት ለጨፌው ቀርቦ ይጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል።
የፍትሕ ተደራሽነትን ለማረጋገጥና ዘርፉን በብቁ የሰው ኃይል ለማደራጀት፤ ተመልምለው ሥልጠናቸውን ያጠናቀቁ ዳኞች ሹመት በጨፌው እንደሚጸድቅም አክለዋል።
በአዳማ ገልመ ጨፌ የሚካሄደው ጉባኤ ከነገ ጀምሮ ለሁለት ቀናት እንደሚቆይም አፈ ጉባኤዋ ጨምረው አመልክተዋል።