በአዲስ አበባ የተገነቡ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ታዳጊዎች የክረምት ወራትን በክህሎት ማጎልበቻ እንዲያሳልፉ ዕድል ፈጥረዋል - ኢዜአ አማርኛ
በአዲስ አበባ የተገነቡ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ታዳጊዎች የክረምት ወራትን በክህሎት ማጎልበቻ እንዲያሳልፉ ዕድል ፈጥረዋል
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 11/2018(ኢዜአ)፦ በአዲስ አበባ የተገነቡ የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎች የክረምት ጊዜያቸውን በአግባቡ በመጠቀም ተሰጥኦዋቸውን ለማዳበር ትልቅ እድል እንደፈጠረላቸው ታዳጊዎች ገለጹ።
መንግስት ለስፖርት ልማት ዘርፍ በሰጠው ልዩ ትኩረት የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችን በየደረጃው በመገንባት ለአገልግሎት አብቅቷል፡፡
በአዲስ አበባ ብቁና ተወዳዳሪ ስፖርተኞችን ማፍራት የሚያስችሉ ውጤታማ የስፖርት ማዕከላትና የማዘውተሪያ ስፍራዎች ተገንብተዋል።
በተገነቡት ከ2ሺህ 580 በላይ የስፖርት ማዘውተሪያና ማሰልጠኛ ማዕከላት ብቃት ያላቸውን ታዳጊ ስፖርተኞች ማፍራት የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑም ተመላክቷል፡፡
እነኚህ ዘመናዊና ደረጃቸውን የጠበቁ የስፖርት ማዘውተሪያዎች ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ውድድሮችን የምታስተናግድበት አቅም መፍጠራቸውም ተገልጿል፡፡
በመዲናዋ በርካታ የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎች መስፋፋታቸው ወጣቶችና ታዳጊዎች በተሻለ ስብዕና እንዲገነቡ የሚያስችሉ ብሎም አልባሌ ቦታዎች ከመዋል የታደጉ ናቸው፡፡
ኢዜአ በአዲስ አበባ በተገነቡ የተለያዩ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ተዘዋውሮ ያነጋገራቸው ታዳጊዎች ከዚህ ቀደም በአካባቢያቸው ምቹ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ባለመኖራቸው ለስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ይቸገሩ እንደነበር ይናገራሉ።
ታዳጊ እያብ ገብረስላሴ እንደሚለው፣ ቀደም ሲል በአካባቢው የነበሩት ሜዳዎች ለስፖርት እንቅስቃሴ አመቺ ስላልነበሩ ተሰጥዖውን ለማዳበር ተቸግሮ እንደነበር ይናገራል።
አሁን ላይ በመዲናዋ በተለያዩ አካባቢዎች የተገነቡት ዘመናዊ የስፖርት ማዘውተሪያዎች፣ ታዳጊዎች ተሰጧቸውን በነፃነት የሚያዳብሩበትና ብቃታቸውን የሚያሳድጉበት ምቹ ሁኔታ መፍጠራቸውን ይገልጻል።
ታዳጊ አብርሃም ታረቀኝ እና አማኑኤል ተስፋ በበኩላቸው፣ ቀደም ሲል የነበሩት ሜዳዎች ለጉዳት ይዳርጉ እንደነበር አስታውሰው፤ አሁን ግን መንግስት ምቹ ሜዳዎችን በመገንባቱ ያለምንም ስጋት በመለማመድ አቅማቸውን እየገነቡ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
ሜዳዎቹ በክረምትም ሆነ በበጋ እንዲሁም ምሽትን ጨምሮ አገልግሎት የሚሰጡ በመሆናቸው ለስፖርታዊ እንቅስቃሴ ትልቅ ሚና እንዳላቸውም ተናግረዋል፡፡
የታዳጊዎች አሰልጣኝ የሆኑት ዮናስ እስክንድር፣ በመዲናዋ የተገነቡት የስፖርት ማዘውተሪያዎች ለታዳጊዎች የመዝናኛና የክህሎት ማሳደጊያ ምቹ መድረክ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በተለይም በክረምት ወራት ተማሪዎች ጊዜያቸውን በአግባቡ እንዲጠቀሙ በማስቻል፣ በስፖርት የታነጸ ጤናማ ትውልድ ለመቅረጽ ትልቅ ፋይዳ እንዳላቸው አስረድተዋል።
የአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ የስፖርት ስልጠና ዳይሬክተር ጎሳዬ አለማየው፣ መንግስት ባለፉት ዓመታት የስፖርት ዘርፉን ለማሳደግ ዘርፈ ብዙ ተግባራት ማከናወኑን አስታውቀዋል።
በመዲናዋ በተገነቡት ዘመናዊ የስፖርት ማዘውተሪያዎች አማካኝነትም፣ ታዳጊዎች ክህሎታቸውን አዳብረው በስፖርት የታነጹ እንዲሆኑ ትልቅ ሚና እየተጫወቱ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በዘንድሮ የክረምት ወራት ከ67 ሺህ በላይ ታዳጊዎችን በበጎ ፈቃድ በማሰልጠን ጊዜያቸውን በአግባቡ እንዲጠቀሙና መሰረታዊ የስፖርት ክህሎት እንዲወስዱ እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።
በስልጠናው ወቅት ከፍተኛ ክህሎት ያሳዩ ታዳጊዎች ወደ በጋው የታዳጊ ወጣት መርሃ ግብር እንዲቀላቀሉ እንደሚደረግ ጨምረው ተናግረዋል።