የገቢ አማራጮችን በማስፋትና ያሉትን አቅሞች በአግባቡ በመጠቀም ለላቀ የልማት ስኬት መዘጋጀት አለብን - ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ - ኢዜአ አማርኛ
የገቢ አማራጮችን በማስፋትና ያሉትን አቅሞች በአግባቡ በመጠቀም ለላቀ የልማት ስኬት መዘጋጀት አለብን - ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ
ሀረር፤ ሐምሌ 11 /2018 (ኢዜአ)፡- የገቢ አማራጮችን በማስፋትና ያሉትን አቅሞች በአግባቡ በመጠቀም ለላቀ የልማት ስኬት ልንዘጋጅ ይገባል ሲሉ የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ገለጹ።
የሐረሪ ክልል የ2018 የገቢ እቅድ ማጠቃለያና የ2019 በጀት አመት የገቢ ንቅናቄ ማስጀመሪያ መድረክ ተካሂዷል፡፡
በመድረኩ ላይ የተገኙት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ፤ በክልሉ የገቢ አማራጮችን በማስፋትና ያሉትን አቅሞች በአግባቡ በመጠቀም ለላቀ የልማት ስኬት ልንዘጋጅ ይገባል ብለዋል።
በክልሉ የሚሰበሰበው ገቢ ካለፉት ዓመታት አንጻር የተሻለ ቢሆንም ገና ብዙ መስራት ይጠበቅብናል ያሉት ርእሰ መስተዳድሩ ግብርን በታማኝነትና በቅንነት የመክፈል ባህል ማደግ አለበት ብለዋል።
በታማኝነት የሚጠበቅባቸውን ግብር ሲከፍሉ የነበሩና ለስኬቱ የሚጠበቅባቸውን ሃላፊነት የተወጡ ባለድርሻ አከላት አስተዋጽዎ ከፍተኛ እንደነበር አስታውሰዋል።
በ2019 በጀት ዓመት የተያዘውን እቅድ ስኬታማ ለማድረግ ዘመናዊ አሰራሮችን በማጎልበት፣ ህገ ወጥ ንግድና ታክስ ስወራን በመከላከል ለተሻለ የልማት ስኬት መትጋት አለብን ብለዋል።
የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ሃላፊ ያሲን አብዱላሂ ፤ ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ገቢ አሟጦ በመሰብሰብ የታቀዱ የልማት ስራዎችን ለማሳካት ጥረት መደረጉን አንስተው በቀጣይም ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ ተናግረዋል።
በ2018 በጀት ዓመት ከተለያዩ ርዕሶች ከ4 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ በመሰብሰብ የእቅዱን 99 በመቶ ማሳካት ስለመቻሉ አንስተው በተያዘው በጀት ዓመትም እቅዱን ለማሳካት በቅንጅት ይሰራል ብለዋል።
በበጀት ዓመቱ በክልሉ ቀጥተኛና ቀጥተኛ ካልሆነ ታክስ፣ ከመዘጋጃ ቤት አገልግሎትና ከሌሎች ከ6 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ ወደ ስራ መገባቱን ተናግረዋል።
በመድረኩ ላይ የክልሉ አመራር አካላት ግብር ከፋዮችና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች የተገኙ ሲሆን ለታማኝ ግብር ከፋዮችም እውቅና ተሰጥቷል።