ቀጥታ፡

ሃገራዊ ምክክሩ ልዩነቶችን በመፍታት ሰላምና ልማትን በተሻለ መልኩ ለማረጋገጥ መሰረት የሚጥል ነው

ደሴ፤ ሐምሌ 10/2018(ኢዜአ)፡-እየተካሄደ ያለው  ሀገራዊ ምክክር ልዩነቶችን በመፍታት ሰላምና ልማትን በተሻለ መልኩ ለማረጋገጥ መሰረት የሚጥል ነው ሲሉ የደሴ ከተማ የሀገር ሽማግሌዎችና ነዋሪዎች ገለጹ።

ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከሁሉም የሀገሪቷ ክፍሎች ባሰባሰባቸው ስምንት አንኳር አጀንዳዎች ላይ በአዲስ አበባ የምክክር ጉባኤ በመካሄድ ላይ ይገኛል።

የጉባኤው መክፈቻ ላይ በመገኘት ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፤ በችግሮች ውስጥ እድሎች ያሉ በመሆኑ የምክክሩን ታሪካዊ እድል በመጠቀም የፀናች፣የለማችና ለዜጎቿ የምትመች ሀገር መገንባት አለብን ብለዋል።

ምክክሩን አስመልከቶ ኢዜአ በደሴ ከተማ ያነጋገራቸው የሀገር ሽማግሌ  አቶ መሀመድ ሰይድ እንዳሉት ፤ እየተካሄደ ያለው ምክክር ልዩነቶችን በመፍታት በሀገሪቱ ሰላምና ልማትን በተሻለ መልኩ ለማረጋገጥ መሰረት የሚጥል ነው ብለዋል።

የተጀመረው ጉባኤ ምክክሮችን በማድረግ ቅድሚያ ለሀገር አንድነት፣ ሰላምና እድገት ለመስጠት ምቹ መደላድል እንዲኖር ከማድረግ አንፃር ተስፋ የሚጣልበት መሆኑንም ነው የገለጹት።

ሌላው የከተማው ነዋሪ አቶ መሀመድ አሊ በበኩላቸው፣ሀገራዊ ምክክሩ ለቀጣዩ ትውልድ ሉዓላዊነቷን የጠበቀች እና ጠንካራ ሀገረ መንግስት የገነባች ኢትዮጵያን ለማስረከብ የሚያስችል  ነው ብለዋል ።

በተጨማሪም ሀገራዊ ምክክሩ አንድነታችንና ሰላማችንን ጠብቀን ዘላቂ ብልጽግናን ለማረጋገጥ የሚያስችል በመሆኑ ለስኬቱ ሁሉም የድርሻውን መወጣት ይጠበቅበታል ነው ያሉት።

ጉባኤው ለኢትዮጵያ አንድነትና ሰላም ቅድሚያ ትከረት በመስጠት ሰላምን ለማጽናት የተሻለ አማራጭ እንደሆነም ተናግረዋል።

የምክክር ኮሚሽኑ እስካሁን ያለፈባቸውን ሂደትና እያከናወናቸው ያሉ ተግባራትን ያደነቁት አቶ መሀመድ፣ ይህም  ውጤቱ ያማረ እንደሚሆን የሚያመላክት መሆኑንም አስገንዝበዋል።

ምክክሩ ችግሮችን በውይይት በመፍታት ህብረ ብሄራዊ እንደነታችንና ሰላማችን ለማጽናት መሰረት የሚጥል ነው ያሉት ደግሞ ወይዘሮ እረህመት አየለ ናቸው።

ምክክሩ በሀገሪቱ ለቆዩ እና ሲንከባለሉ ለመጡ ውስብስብ ችግሮቻችን መፍትሄ የሚሰጥ መሆኑን ጠቁመው፣ አሁን የደረሰበት ደረጃም የሚደነቅና ውጤታማ መሆን የሚያስችል ነው ብለዋል።

ምክክሩ  ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግና ሀገራችንን የሚያጸና ይሆናል የሚል እምነት እንዳላቸው አስተያየት ሰጪዎቹ ገልጸዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም