ቀጥታ፡

በዞኑ ሰላምን ይበልጥ በማፅናት፣ የተጀመሩ የልማት ስራዎችን ለማስቀጠል የበኩላችንን እንወጣለን

ጭሮ፤ሐምሌ 11/2018(ኢዜአ)፡-በምዕራብ ሐረርጌ ዞን ሰላምን ይበልጥ በማፅናት፣ የተጀመሩ የልማት ስራዎችን ለማስቀጠል የበኩላችንን እየተወጣን ነው ሲሉ የዞኑ አባገዳዎችና የአገር ሽማግሌዎች ገለጹ።

ኅብረተሰቡ የአካባቢውን ሰላም በባለቤትነት እንዲጠብቅ በተከናወኑ ተግባራት ውጤታማ ሥራ መሠራቱን የዞኑ ሰላምና ፀጥታ ጽሕፈት ቤት አስታውቋል።

የጭሮ ከተማ አባገዳ ሐሺም አብደላ በሰጡት አስተያየት፤ በዞኑ ያለውን አስተማማኝ ሰላም ዘላቂ በማድረግ ረገድ ኅብረተሰቡን በማስተባበር የበኩላቸውን እየተወጡ ነው።

ዞኑ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በተለይ በግብርናው መስክ እያስመዘገበ ያለው ስኬት በአስተማማኝ ሰላም ላይ የተመሠረተ መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህንን ውጤት ለማስቀጠል በተለይ ወጣቶች የላቀ ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል።

የሸነን ዱጎ ወረዳ አባገዳ አህመድ አሚን በበኩላቸው፣ በአካባቢው ለሰፈነው አስተማማኝ ሰላም ዋነኛው ምንጭ ሕዝቡ ከመንግሥት ጎን በመቆም የአካባቢውን ፀጥታ በትጋት በመጠበቁ መሆኑን ገልጸዋል።

ይህም የልማት እንቅስቃሴው በየዓመቱ እያደገ እንዲመጣ ትልቅ አስተዋጽኦ ማድረጉን ጠቁመው፣ ኅብረተሰቡ የሰላምን ጠቀሜታ በመረዳት የሚጠበቅበትን እንዲወጣ የራሳቸውን አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑን ተናግረዋል።

የሰላም ባለቤት ሕዝብ መሆኑን በመገንዘብ የሰፈነው ሰላም ዘላቂ እንዲሆን ድርሻቸውን እየተወጡ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የመሰላ ከተማ የአገር ሽማግሌ ሼህ ሲራጅ መሐመድ ናቸው።

እንደ አገር ሽማግሌና የሃይማኖት አባትነታቸውም ለኅብረተሰቡ አስፈላጊውን ግንዛቤ በመስጠት ረገድ የሚጠበቅባቸውን ሚና አጠናክረው እንደሚወጡ ተናግረዋል።

የምዕራብ ሐረርጌ ዞን ሰላምና ፀጥታ ጽሕፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ አብዲ ዋቆ በበኩላቸው፣ በዞኑ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ በተሠራው የተቀናጀ ሥራ አስተማማኝ ሰላም ማረጋገጥ መቻሉን ገልጸዋል።

በተለይ ወጣቱ የሰላምን ዋጋ ተረድቶ አካባቢውን በንቃት በመጠበቅ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን የገለጹት ምክትል ኃላፊው፣ በዚህም በዞኑ የመሠረተ ልማት አውታሮች እየተስፋፉና የግብርና ልማት ሥራዎች ውጤታማ እየሆኑ መምጣታቸውን አስገንዝበዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም