ቀጥታ፡

በዓለም ዋንጫው ማን ሶስተኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቅቃል? ፈረንሳይ ወይስ እንግሊዝ?

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 11/2018 (ኢዜአ)፦  በ23ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ ፈረንሳይ እና እንግሊዝ  ሶስተኛ ደረጃ ይዞ ለመጨረስ ዛሬ ይጫወታሉ።

የሁለቱ ሀገራት ጨዋታ ከሌሊቱ ስድስት ሰዓት ላይ በሚያሚ ስታዲየም ይከናወናል።

በግማሽ ፍጻሜው ፈረንሳይ በስፔን የ2 ለ 0፣ እንግሊዝ በአርጀንቲና የ2 ለ 1 ሽንፈት አስተናግደዋል።

ዓለም ዋንጫውን ታነሳለች ተብላ ተጠብቃ የነበረቸው ፈረንሳይ በስፔን ያስተናገደችው ሽንፈት እና ያሳየችው አቋም ያልተጠበቀ ሆኗል።

እንግሊዝ በግማሽ ፍጻሜው እስከ ጨዋታው መገባዳጃ ድረስ 1 ለ 0 እየመራች ብትቆይም በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች የተቆጠሩባት ጎሎች ፍጻሜ የመድረስ ህልሟ እንዳይሳካ አድርጎታል።

ሁለቱ ሀገራት ለተመኙት የፍጻሜ ጨዋታ ባይደርሱም ውድደሩን ሶስተኛ ደረጃን ይዘው ለማጠናቀቅ ይፋለማሉ።

ብሔራዊ ቡድኖቹ በዓለም ዋንጫው እርስ በእርስ ሲገናኙ የአሁኑ ለአራተኛ ጊዜ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።

እንግሊዝ እ.አ.አ በ1966 ባሰናዳችው ስምንተኛው የፊፋ የዓለም ዋንጫ በምድብ መርሐ ግብት ተገናኝተው አዘጋጇ ሀገር 2 ለ 0 አሸንፋለች።

በወቅቱ እንግሊዝ ዋንጫውን በማንሳት ብቸኛ የመድረኩ ክብሯን አግኝታለች።

እ.አ.አ በ1982 በስፔን በተካሄደው 12ኛው የፊፋ የዓለም ዋንጫ በድጋሚ በምድብ ደረጃ ተገናኝተው እንግሊዝ 3 ለ 1 አሸንፋለች።

ኳታር እ.አ.አ በ2022 ባዘጋጀችው 22ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ በሩብ ፍጻሜው ባደረጉት ጨዋታ ፈረንሳይ 2 ለ 1 በማሸነፍ ዋንጫውን አንስታለች።

ፈረንሳይ በውድድሩ ለፍጻሜ ብትደርስም በአርጀንቲና ተሸንፋለች።

ሁለቱ ሀገራት የዓለም ዋንጫውን ጨምሮ በውድድር እና በወዳጅነት ጨዋታዎች 32 ጊዜ ተገናኝተዋል።

እንግሊዝ 17ቱን በማሸነፍ የበላይነቱን ይዛለች። ፈረንሳይ በ10ሩ ድል ሲቀናት በቀሪ አምስት ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል።

በ32ቱ ጨዋታዎች ላይ እንግሊዝ 72፣ ፈረንሳይ 41 ጎሎችን ከመረብ ላይ አሳርፈዋል።

ፈረንሳይ ለዓለም ዋንጫው ባታልፍም በዘንድሮው ውድድር ድንቅ ብቃቱን ያሳየው የ27 ዓመቱ ኪሊያን እምባፔ በጨዋታው ይጠበቃል።

ምባፔ በዘንድሮው የዓለም ዋንጫ ስምንት ጎሎችን በማስቆጠር እና ሶስት ለግብ የሚሆኑ ኳሶችን በማቀበል ከአርጀንቲናው ሊዮኔል ሜሲ ጋር በጎል እኩል ሆኑ ብዙ ኳስ ባቀበለ በሚለው መለያ (በአንድ ተበልጦ) በኮከብ ግብ አስቆጣሪነቱ ፉክክር ሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

በአጠቃላይ በውድድሩ ላይ 20 ጎሎች ከመረብ ላይ በማሳረፍ በምንጊዜም ከፍተኛ አስቆጣሪነት ዝርዝር ከሜሲ (21 ጎል) በአንድ አንሶ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

ምባፔ በዓለም ዋንጫው የጥሎ ማለፍ ምዕራፍ 12 ጎሎችን በማስቆጠር በውድድሩ አዲስ ክብረ ወሰን አስመዝግቧል።

ፈረንሳዊው አጥቂ በዛሬው ጨዋታ ግቦች ካስቆጠረ ኮከብ ግብ አግቢ ሆኖ የማጠናቀቅ እድል ይኖረዋል።

በዘንድሮው የዓለም ዋንጫ አምስት ጎሎችን ከመረብ ላይ ያሳረፈው ኡስማን ዴምቤሌ እና አምስት ለግብ የሚሆኑ ኳሶችን ያቀበለው ማይክል ኦሊሴም ልዩነት ፈጣሪ ተጫዋቾች ናቸው።

ከእንግሊዝ በኩል በዘንድሮው የዓለም ዋንጫ በተመሳሳይ ስድስት ግቦችን ያስቆጠሩት ጁድ ቤሊንግሃም እና ሃሪ ኬን ይጠበቃሉ። ሁለቱ ተጫዋቾች በኮከብ ግብ አስቆጣሪነቱ ተፎካካሪ ናቸው።

ፈረንሳይ ከዚህ ቀደም በሁለት የዓለም ዋንጫዎች (እ.አ.አ 1958 እና 1986) ሶስተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።

እንግሊዝ ከዚህ ሁለት ጊዜ (እ.አ.አ በ1990 እና 2018) ሶስተኛ ደረጃን ይዛ ለማጠናቀቅ ተጫዋውታ ሽንፈት አስተናግዳለች።

የሁለቱ ሀገራት ጨዋታ ተመጣጣኝ ፉክክር ይታይበታል ተብሎ ይጠበቃል።

የ42 ዓመቱ ቬንዙዌላዊ ጄሱስ ኖኤል ቫለንዝዌላ ሳኤዝ ጨዋታውን በመሐል ዳኝነት እንዲመሩት ተመድበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም