ቀጥታ፡

በነቀምቴ ከተማ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ብልሹ አሰራርን እያስቀረ ነው

ነቀምቴ፤ ሐምሌ 11/2018(ኢዜአ)፦ የነቀምቴ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የተገልጋዩን እንግልትና ብልሹ አሰራርን እየቀረፈ መሆኑን ኢዜአ ያነጋገራቸው የከተማዋ ነዋሪዎች ገለጹ።

ከከተማዋ ነዋሪዎች መካከል ሻምበል ኦላና ጉደታ፤ መንግስት የአገልግሎት አሰጣጡን ለማዘመን መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን ማስጀመሩ እጅግ ጠቃሚ ሆኖ እንዳገኙት ተናግረዋል።


 

ይህ አሰራር የምንፈልገውን አገልግሎት በአጭር ጊዜ እንድናገኝ እያገዘን ነው ያሉት ነዋሪው፣ በተለይም ቀደም ሲል በአንዳንድ መስሪያ ቤቶች የነበረው የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር አሁን መቀረፉን ገልጸዋል።


 

ሌላኛው ነዋሪ አቶ ተመስገን ነጋሽ፤ በመንግስት መስሪያ ቤቶች የነበሩ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮች የረጅም ጊዜ የመልካም አስተዳደር ጥያቄያችን ነበር ብለዋል።

በመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ከዚህ ቀደም ይታዩ የነበሩ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን ቀርፏል ነው ያሉት።

መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎቱ ተገልጋዩ ጊዜውን፣ ጉልበቱንና ገንዘቡን እንዳያባክን እያበረከተ ያለው አስተዋጽኦ የላቀ መሆኑን የገለጹት ደግሞ አቶ ደገፉ ቶለሳ ናቸው።

ከዚህ ቀደም ረጅም ጊዜ ይውስዱ የነበሩ መንግስታዊ አገልግሎቶች በአጭር ጊዜ መፍትሄ ሲያገኙ መመልከታቸውንም ተናግረዋል።


 

የነቀምቴ ከተማ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ኃላፊ በየነ ቀናቴ በበኩላቸው፤ በማዕከሉ የሚሰጡ አገልግሎቶች ቀልጣፋ እንዲሆኑ በትኩረት እየተሰራ ሲሆን፣ አጠቃላይ ሂደቱም በቴክኖሎጂ የተደገፈ ነው ብለዋል።

ይህንን ስራ ውጤታማ ለማድረግ በማዕከሉ 25 የተለያዩ ተቋማት ተካተው አገልግሎት እየሰጡ ሲሆን 117 ሰራተኞችም መመደባቸውን ገልጸዋል።

በአጠቃላይ በማዕከሉ 98 የተለያዩ የአገልግሎት አይነቶች እየተሰጡ መሆኑን ጠቅሰው፣ ማዕከሉ ስራ ከጀመረ ወዲህ ተገልጋዩ ጉዳዩን በአጭር ጊዜ እየፈጸመ ወደ መደበኛ ስራው እየተመለሰ ይገኛል ብለዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም