ኢትዮጵያ የአፍሪካ፣ ካሪቢያንና ፓሲፊክ አገራት ድርጅት (አካፓድ) ሊቀመንበር ሆና ተመረጠች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የአፍሪካ፣ ካሪቢያንና ፓሲፊክ አገራት ድርጅት (አካፓድ) ሊቀመንበር ሆና ተመረጠች
አዲስ አበባ፤ሐምሌ 10/2018 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ የአፍሪካ፣ ካሪቢያንና ፓሲፊክ አገራት ድርጅት (አካፓድ) ሊቀመንበር ሆና ተመርጣለች።
121ኛው የአካፓድ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ስብሰባ ሐምሌ 8-9 ቀን 2018 ዓ.ም. ቤልጅየም መዲና ብራስልስ ተካሂዷል።
በጉባኤው ላይ በገንዘብ ሚኒስትር ዲኤታ ሰመሪታ ሰዋሰው የተመራ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የስራ ኃላፊዎችን ያካተተ የልኡካን ቡድን ኢትዮጵያን በመወከል ተሳትፏል።
የሚኒስትሮቹ ስብሰባ የትኩረት አጀንዳዎች የማላቦ ዲክላሬሽን አተገባበር ሂደትን መገምገም፣ የድርጅቱን የፋይናንስ አቅም በዘላቂነት ለመገንባት ስለሚወሰዱ እርምጃዎች መምከር ላይ ያተኮረ ነው።
እንዲሁም የድርጅቱ ማሻሻያ ሂደት ያለበትን ደረጃ መገምገም፣ የሳሞአ ስምምነትን የትግበራ ሂደት መገምገም እንዲሁም ሌሎች የድርጅቱንና የአባል ሀገራትን ጥቅም ስለሚያስጠብቁ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት ተደርጓል።
ኢትዮጵያ አቋሟን የሚያንጸባርቁ እና ድርጅቱን በፕሬዚዳንትነት በምትመራበት ወቅት የምትከተላቸውን የትኩረት አቅጣጫዎች የሚያመለክቱ ንግግሮች አቅርባለች።
በጉባኤው ማጠናቀቂያም ኢትዮጵያ ከኦገስት 1 ቀን 2026 እስከ ጃንዋሪ 31 ቀን 2027 የአፍሪካ፣ ካሪቢያንና ፓስፊክ አገራት ድርጅት የሚኒስትሮች ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሆና ተመርጣለች።
ኢትዮጵያ በቀጣይ ስድስት ወራት የጉባኤው ሰብሳቢነቷ ወቅት ቅድሚያ የምትሰጣቸውን የትኩረት ጉዳዮች አስተዋውቃለች።
እነዚህም ከወቅቱ ጂኦፖለቲካዊ እውነታ አኳያ የድርጅቱን ጽ/ቤትና የአባል አገራትን የፖሊሲ ነጻነት ማረጋገጥ፣ በራስ አቅም ሊከናወኑ ስለሚችሉ የልማት ስራዎችና የአገር ውስጥ ሃብት ማሰባሰብ የኢትዮጵያን ተሞክሮ በማጋራት በምሳሌነት መምራት፣ በተቋሙ ውስጥ ግልጽነትና ተጠያቂነት እንዲጠናከር በማድረግ የመልካም አስተዳደር ችግር እንዲወገድ መስራት፣ የድርጅቱ የፋይናንስ እጥረት በዘላቂነት እንዲፈታ የተጀመረው የሀብት ማሰባሰብ ጥረት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ማድረግ እና የአውሮፓ ህብረት እና የአካፓድ ግንኙነት መሠረት የሆነው የሳሞአ ስምምነት አፈጻጸም በተሻለ መልኩ እንዲጓዝ መስራት ዋና ዋናዎቹ ናቸው።
ኢትዮጵያ ድርጅቱ ከተመሰረተ እ.ኤ.አ. 1975 ጀምሮ ሁለት ጊዜ (እ.ኤ.አ. ከነሀሴ 1 ቀን 1986 እስከ ጥር 31 ቀን 1987 እና ከየካቲት 1 ቀን 2017 ዓ.ም. እስከ ሀምሌ 31 ቀን 2017 ) ተቋሙን በሰብሳቢነት ማገልገሏን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገልጿል።
በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ የአካፓድ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሰብሳቢ ሆና መመረጧ፣ በዓለም አቀፍ መድረክ ያላትን የዲፕሎማሲ ተፅዕኖ ፈጣሪነት በድጋሚ የሚያረጋግጥ ታላቅ ስኬት መሆኑም ተገልጿል።
ይህ ታሪካዊ ኃላፊነት ኢትዮጵያ በደቡብ-ደቡብ ሁለንተናዊ ትብብር ላይ ያላትን ተሳትፎ ይበልጥ ከማጠናከሩ ባሻገር፣ ከአባል አገራቱና ከአውሮፓ ህብረት ጋር የሚደረጉ ትብብሮችን በበላይነት ለመምራት፣ ብሄራዊ ጥቅሟን ለማስከበር እና መልካም ገፅታዋን ለመገንባት የዲፕሎማሲ ዕድሎችን ይከፍታል።
ጉባኤውም ለኖቬምበር 2026 ዓ.ም. የታቀደው የ122ኛው የአካፓድ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ስብሰባ በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት አዲስ አበባ እንዲካሄድ በድርጅቱ አባል ሀገራት ተወስኖ ተጠናቋል።