ቀጥታ፡

ሕገ-ወጡ የሕወሓት ቡድን የትግራይን ሕዝብ ለከፋ ጉዳት የዳረገ የጥፋት ተግባር ላይ ተሰማርቷል

አዲስ አበባ ፤ ሐምሌ 10/2018 (ኢዜአ) ፦ ሕገ-ወጡ የሕወሓት ቡድን ሻዕቢያን ጨምሮ ከተለያዩ ሕገ-ወጥ ኃይሎች ጋር በመጣመር የትግራይን ሕዝብ ለከፋ ጉዳት የሚዳርግ የጥፋት ተግባር ላይ በመሰማራት ጠላትነቱን አረጋግጧል ሲሉ የትግራይ ክልል የቀድሞው ርዕሰ መስተዳድርና የዓረና ለሉዓላዊነትና ዴሞክራሲ ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ገብሩ አስራት ገለጹ።

የትግራይ ክልል የቀድሞ ርዕሰ መስተዳድር እና የዓረና ለሉዓላዊነትና ዴሞክራሲ ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ገብሩ አስራት በወቅታዊ የትግራይ ሁኔታ ላይ ከፐልስ ኦፍ አፍሪካ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

በቆይታቸውም ሕገ-ወጡ የሕወሃት ቡድን ፖለቲካዊና ወታደራዊ መሪዎች የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት ወደ ጎን በመተው፣ በስምምነቱ መሰረት የተቋቋመውን ጊዜያዊ አስተዳደር እንዳይሠራ በማድረግና በማፍረስ የክልሉን ሥልጣን በኃይል ተቆጣጥሮ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ሕገ-ወጡ የሕወሃት ቡድን ለሥልጣን ሲል ከትግራይ ሕዝብ ታሪካዊ ጠላቶች፣ ከሻዕቢያና ከሌሎች የውጭና የሀገር ውስጥ ቡድኖች ጋር በመተባበር ለሌላ ግጭት እየተዘጋጀ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።

ሻዕቢያ የትግራይን ሕዝብ ለማጥፋት ይጥራል ያሉት የፓርቲው ሥራ አስፈጻሚ አቶ ገብሩ፤ ለዚህ ደግሞ ቀደም ብሎ በክልሉ የፈጸመው ጭፍጨፋ እና ያስከተለው ውድመት ማረጋገጫ ነው ብለዋል።

የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ሻዕቢያ የትግራይን ሕዝብ ለማጥፋት የነበረውን ሕልም እንዳከሸፈበት ተናግረው፤ ስምምነቱ ሲፈረምም 'ተሰናክለናል' ሲል በአደባባይ መግለጹን አስታውሰዋል።

ሕገ-ወጡ የሕወሃት ቡድን አሁንም ትግራይን የግጭት ማዕከል ለማድረግ ከተለያዩ ሕገ-ወጥ ኃይሎች ጋር በመጣመር የትግራይን ሕዝብ ለመጉዳት እየሠራ መሆኑን አስረድተዋል።

ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱ ከውጭ ሀገራት ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የመመስረት ሥልጣን ለፌዴራል መንግሥት ብቻ መሆኑን እንደሚደነግግ ያስታወሱት አቶ ገብሩ፤ ሕገ-ወጡ የሕወሃት ቡድን ከኤርትራ፣ ከሱዳን እና ከሌሎች ሀገራት ጋር እያደረገ ያለው ግንኙነት ሕጋዊ መሠረትና አግባብነት እንደሌለው ገልጸዋል።

ይህ ሕገ-ወጥ ቡድን ካለፈው ስህተቱ መማር ያልቻለና የማይማር መሆኑን ጠቁመው፤ ቡድኑ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ታሪካዊ ጠላት ከሻዕቢያ ጋር በመተባበርና ጥምረት በመፍጠር እኩይ ድርጊቶችን እየፈጸመ መሆኑን ገልጸዋል።

በተግባር ተፈትነው ለውድቀት የተዳረጉት እነዚህ ኃይሎች፣ ምንም ዓይነት የፖለቲካም ሆነ የርዕዮተ-ዓለም ለውጥ ሳያደርጉ ባረጀ አስተሳሰባቸው መጓዛቸው ለትግራይ ሕዝብ ምንም ዓይነት ፋይዳ ሊያስገኝ እንደማይችል አስረድተዋል።

ሕገ-ወጡ ቡድን ባወጣው ሕገ-ወጥ አዋጅ ምክንያት የትግራይ ሕዝብ በከባድ ቀውስና በደል ውስጥ እንደሚገኝና የትግራይ ወጣትም ሀገሩን ትቶ እየተሰደደ መሆኑን ተናግረዋል።

ሕገ-ወጡ የሕወሃት ቡድን ካለፈው የአፋኝነቱ፣ የጭቆና እና የአምባገነንነት ተግባሩ ባደረሰው በደል ያልተጸጸተ መሆኑን አመልክተው፤ አሁን ደግሞ ዝርፊያን እና ቅሚያን መሠረት ያደረገ አስተዳደር በመዘርጋት የክልሉን ሕዝብ ለከፍተኛ ችግር እየዳረገ መሆኑን አስረድተዋል።

ወጣቶችን በማፈን እና ታጣቂዎችን ወደ ሱዳን በመሸጥ ገቢ እየሰበሰበ እንደሚገኝ ገልጸው፤ ይህም የቡድኑን የጥፋት ተልዕኮ መገለጫዎች በግልጽ የሚያሳይ መሆኑን አስረድተዋል።

መላው የትግራይ ሕዝብ እያደረገ ያለውን ሰላማዊ ትግል አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ጠቅሰው፤ ለትግራይ ችግር ዋና መፍትሔው ወደ ፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት መመለስ መሆኑን ጠቁመዋል።

ነገር ግን ቡድኑ በብዙ መንገድ ተጠያቂ የሚያደርጉት በርካታ በደሎችን ማድረሱና በሕገ-ወጥ ተግባራት ላይ በመዘፈቁ ምክንያት ሰላምን ቀዳሚ ምርጫው ያደርጋል የሚል እምነት እንደሌላቸው ተናግረዋል።

ሕገ-ወጡ ቡድን በፈጸማቸው ተደጋጋሚ ድርጊቶች ምክንያት ለሕግ ተጠያቂ የሚሆንበት ዕድል ሰፊ መሆኑንም አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም