የጭስ አልባ ትራንስፖርት ዘርፍን ለማስፋፋት ከዓለም ባንክ ጋር በአጋርነት ለመሥራት ተስማምተናል-ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
የጭስ አልባ ትራንስፖርት ዘርፍን ለማስፋፋት ከዓለም ባንክ ጋር በአጋርነት ለመሥራት ተስማምተናል-ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 10/2018 (ኢዜአ)፦የአዲስ አበባ ከተማን የትራንስፖርት አገልግሎት ይበልጥ ለማሻሻል ከዓለም ባንክ ጋር በጋራ ለመሥራት የሚያስችል ፍሬያማ ውይይት ማድረጋቸውን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
ከንቲባ አዳነች በዓለም ባንክ የኢትዮጵያ፣ ኤርትራ፣ ሱዳን እና ደቡብ ሱዳን ዳይሬክተር ከሆኑት ማርያም ሳሊም ጋር ባደረጉት ውይይት፣ ከተማ አስተዳደሩ የትራንስፖርት ዘርፉን ለማዘመን እና በተለይም የጭስ አልባ ትራንስፖርት (E-mobility) ተደራሽነትን በስፋት ለማዳረስ እያከናወነ ባለው ሥራ ዙሪያ በዝርዝር መምከራቸውን ገልጸዋል።
በውይይታቸውም አስተዳደሩ የጀመራቸውን ሥራዎች ይበልጥ ለማጠናከር ያለመ ውይይት ማድረጋቸውን በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ጠቁመዋል።
እንዲሁም በዘርፉ የተሰማሩ የግል ተቋማትን ለመደገፍ ከዓለም ባንክ ጋር በአጋርነት እና በትብብር በጋራ ለመሥራት ተግባብተናል ብለዋል።
ከንቲባ አዳነች ለዳይሬክተሯ ማርያም ሳሊም እና አብረዋቸው ለነበሩት የቴክኒካል ቡድን አባላት በራሳቸው እና በአዲስ አበባ ሕዝብ ስም የላቀ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።