ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ ያስከበረችውን ስትራቴጂክ ጥቅም በቀይ ባሕር የመድገም ሕጋዊና ተፈጥሯዊ መብት አላት

አዲስ አበባ፤ሐምሌ 10 /2018 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ ያስከበረችውን ስትራቴጂክ ጥቅም በቀይ ባሕር የመድገም ሕጋዊና ተፈጥሯዊ መብት አላት ሲሉ አሜሪካዊው የፖለቲካ ተንታኝ አንድሪው ኮሪብኮ ገለጹ።

ሕዳሴ ግድብ ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ውህደትን የሚያፋጥን ስትራቴጂካዊ የልማት ውጤት መሆኑንም አስገንዝበዋል።

አንድሪው ኮሪብኮ እንደገለጹት፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለታችኞቹ ተፋሰስ ሀገራት የተስተካከለ የውሃ ፍሰት በመፍጠር፣የጎርፍ መጥለቅለቅንና የውሃ ብክነትን የታደገ አህጉራዊ ፕሮጀክት ነው።


 

ኢትዮጵያ ግድቡን መገንባቷ ሀገራዊና ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ዕድገትን የሚያፋጥን የኤሌክትሪክ ኃይል ትስስር አቅም እንዲጎለብት ማስቻሉን ተናግረዋል።

በዚህም ለምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የሚላከው የኤሌክትሪክ ኃይል፣ቀጣናዊ ትብብርን በማጎልበት ለአፍሪካ ኢኮኖሚ ውህደት ወሳኝ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብን የገነባችበት መንገድ፣በታችኞቹ ተፋሰስ ሀገራት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ይኖረዋል የሚለውን የግብፅ መሰረተ ቢስ አጀንዳ ሙሉ ለሙሉ የቀለበሰ መሆኑን አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ ያስከበረችውን ስትራቴጂክ ጥቅም በቀጣይም በቀይ ባሕር የመድገም ሕጋዊና ተፈጥሯዊ መብት እንዳላት አብራርተዋል።


 

የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች የሚከተሉት ስትራቴጂ በቀጥታ ሳይሆን በተዘዋዋሪ ግፊትና በተላላኪዎች አማካይነት የሚፈጸም መሆኑን ጠቁመዋል።

ስግብግብ ፍላጎትና በሌሎች ሀገር ላይ የሚጫን ተስፋፊነትን ያነገቡ የግብፅ ገዥ መደቦች በኢትዮጵያ ውስጥና በኤርትራ የሚገኙ ፅንፈኛና ታጣቂ ቡድኖችን እንደ መሳሪያ በመጠቀም የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማደናቀፍ በተደጋጋሚ ሲሞክሩ መስተዋላቸውን አውስተዋል።

ይህ የማያዋጣ አካሄድ መሆኑን በመጠቆም በተፋሰሱ ሀገራት የሚነሱ የውሃ ሀብት አጠቃቀም ጥያቄዎችን፣የአፍሪካን ችግሮች በአፍሪካዊ መፍትሔ በሚል መርህ በሰለጠነ ውይይትና በጋራ ተጠቃሚነት መፍታት እንደሚቻል አስረድተዋል።

የዓባይ የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ውጥረት ከሚያባብስ አካሄድ ሊቆጠቡ ይገባል ያሉት ተንታኙ፥ ቀጣናዊ ሰላምና መረጋጋትን በማስቀደም የጋራ ብልፅግናን የሚያረጋግጥ ትብብር ማድረግ እንደሚኖርባቸው አፅንኦት ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም