ቀጥታ፡

በውጭ ሀገር ተደብቀው በኢትዮጵያዊያን ላይ ኢሰብአዊ ድርጊት ሲፈጽሙ የነበሩ ሕገ-ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ተያዙ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 10/ 2018 (ኢዜአ) ፦ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከተባበሩት አረብ ኢምሬትስ ዱባይ ፖሊስ ጋር በመቀናጀት በውጭ ሀገር ተደብቀው በኢትዮጵያውያን ላይ ኢሰብአዊ ድርጊቶችን ሲፈጽሙ የነበሩ ዳውድ ተፈሪ ለገሰ እና ደስታ ተገኝ አበጋዝ የተባሉ ሕገ-ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታውቋል።

ሁለቱ ዋና ተጠርጣሪዎች የተለያዩ የማታለያ ዘዴዎችን በመጠቀም 105 ዜጎችን በሕገ-ወጥ መንገድ ወደ ዱባይ በመውሰድና ከ188 ሚሊዮን ብር በላይ ከተጎጂዎች በመሰብሰብ፣ በበርካታ ዜጎች ላይ ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰት ሲፈጽሙ የቆዩ በመሆናቸው የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከዱባይ ፖሊስ ጋር በመተባበር በቁጥጥር ሥር ውለው ለሀገራችን ተላልፈው እንዲሰጡ አድርጓል።

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከተባበሩት አረብ ኢምሬትስ ዱባይ የኢትዮጵያ ኤምባሲ በኩል በደረሰው ጥቆማ፣ ተጠርጣሪዎቹ ዱባይ ተቀምጠው ሀገር ውስጥ ባሉ ተባባሪዎቻቸው አማካኝነት ወጣቶችን በመመልመል ወደ ዱባይ በመላክ፣ በተዘጋጀ የማገቻ ቦታ በማቆየት፣ በተለይ በሴቶች ላይ ጥቃት በማድረስና በማሰቃየት ከፍተኛ ወንጀል ሲፈጽሙ የቆዩ መሆናቸው ተረጋግጧል።

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስም ጉዳዩን ሲያጣራ ቆይቶ በሀገር ውስጥና በውጭ ሆነው በተቀናጀ መንገድ ወንጀሉን ሲፈፅሙ በቆዩ ዳውድ ተፈሪ ለገሰ ፣ ደስታ ተገኝ አበጋዝ እና በግብረአበሮቻቸው ላይ የፍርድ ቤት መያዣ ትዕዛዝ በማውጣት፣ ውጭ ሀገር ያሉትን ከዱባይ ፖሊስ ጋር በትብብር በመስራት ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ሥር ውለው ሐምሌ 10 ቀን 2018 ዓ.ም ለሀገራችን ተላልፈው እንዲሰጡ አድርጓል።

ተጠርጣሪዎቹ ምንም ዓይነት ሰውን ወደ ውጭ መላክ የሚያስችል ሕጋዊ ፍቃድ ሳይኖራቸው፣ በሀገር ውስጥ ያለው ቡድን ከውጪ ካለው ቡድን ጋር ትስስር በመፍጠርና በተቀናጀ መልኩ "በተለያዩ ካምፓኒዎች ስራ እናስቀጥራችኋለን’’ በማለት ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ በርካታ ዜጎችን ከተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች በመመልመል፣ ሀሰተኛ መረጃዎችን በማሰራጨትና ያልተገባ ተስፋ በመስጠት ከአንድ ሰው ከ320 ሺህ እስከ 600 ሺህ ብር በመቀበል ማታለያ የቱሪስት ቪዛ አዘጋጅተው በመላክ፣ በሀገር ውስጥ ባሉ ተባባሪዎቻቸው በተከፈተ የባንክ አካውንት ገንዘቡን በኢትዮጵያ ብር፣ በድርሃም እና በሪያል ገቢ የሚያስደርጉ መሆናቸውን ፖሊስ ደርሶበታል።


 

ገንዘቡን የከፈሉ ተጎጂዎች ዱባይ እንደገቡ በጉልበት ሥራ ላይ እንዲሰማሩ በማድረግ፣ ከተጎጂዎች "ኮሚሽን" በሚል ተጨማሪ ገንዘብ በማስከፈል እንዲሁም የሁለት ወር የቱሪስት ቪዛ ሲያልቅ "የሁለት ዓመት የመኖሪያ ፍቃድ እናሰጣችኋለን፤ ካልከፈላችሁ ግን ወደ ኢትዮጵያ ትመለሳላችሁ" በማለት በአንድ ሰው 1 ሺህ 200 ድርሃም እንዲከፍሉ በማድረግ በዜጎች ላይ ከፍተኛ ግፍና ስቃይ ሲያደርሱ ቆይተዋል ብሏል ፖሊስ።

ተጠርጣሪዎቹ ተጎጂዎችን ከዱባይ ኤርፖርት ከተቀበሉ በኋላ ሰዎችን የሚያከማቹበት ቦታ በመውሰድ፣ በአንድ ክፍል ውስጥ በርካታ ወንዶችንና ሴቶችን በማገት፣ ምግብ በስምንት ቀን አንድ ጊዜ ደረቅ ሩዝ በመስጠት ለከፍተኛ ርሃብ እና እንግልት እንዲሁም ሴቶች ላይ ጾታዊ ጥቃት ሲያደርሱባቸው መቆየታቸው ተደርሶበታል።

በተጨማሪ ባደረገው ክትትል፣ በሀገር ውስጥ ሆነው ዱባይ ካሉት ግብረ-አበሮቻቸው በሚሰጣቸው ትዕዛዝ ሰዎችን መልምሎ በመላክና የባንክ አካውንት ከፍተው ገንዘብ እያሰባሰቡ የነበሩ 1ኛ ብዙአየሁ አውግቸው በሀይሉ እና 2ኛ ራህመት አበበ እሸቴ የተባሉ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር አውሎ ምርመራውን በስፋት በማከናወን ላይ መሆኑንም የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ገልጿል።

ፖሊስ ምርመራውን ዘመኑ ያፈራቸውን ቴክኖሎጂዎች ተጠቅሞ ይህንን ውስብስብና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀል ለማጣራት እንዲሁም በእነዚህ ተጠርጣሪዎች አማካኝነት ከሀገር ወጥተው ከፍተኛ ስቃይ ደርሶባቸው ከነበሩ ግለሰቦችና ተጎጂዎች ካሉበት ዱባይ የቀጥታ ቨርቹዋል የምስክርነት ቃላቸውን በመቀበል ላይ እንደሚገኝ ገልጿል።

ፖሊስ ሕጋዊ ፍቃድን ሽፋን በማድረግ ከሕገ-ወጥ አዘዋዋሪዎች ጋር በመመሳጠር ሕገ-ወጥ ተግባር የሚፈጽሙና በዜጎች ከፍተኛ ኢሰብዓዊ ድርጊት የሚፈጽሙ ኤጀንሲዎችም መኖራቸውን ማረጋገጡን ጠቅሶ በቀጣይ ምርመራውን በእነዚህ አካላት ላይም አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በዚህ ውስብስብ ወንጀል ውስጥ በህጋዊ ሽፋን ህገ-ወጥ ተግባር የሚፈጽሙ አካላትን ለመያዝ ከዱባይ ፖሊስና በዱባይ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጋር በቅንጅት በመስራት ህገ-ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ላይ ጠንካራ ክትትል እያደረገ መሆኑን ገልጿል።

ሕገ-ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎችና ተባባሪዎቻቸው በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ ድጋፍ ላደረጉ አካላት ምስጋናውን እያቀረበ፤ ኅብረተሰቡ የዜጎች ተሳትፎ መተግበሪያ (EFPApp)፣ 991 ነፃ የስልክ መስመር እና ሰው አልባ ፖሊስ ጣቢያ (SPS)ን በመጠቀም መረጃ በመስጠት ትብብሩን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አስተላልፏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም