ቀጥታ፡

የፍርድ ቤት መር አስማሚነት ሥርአት ለህብረተሰቡ ፈጣንና ተደራሽ ፍትህ ለመስጠት እያስቻለ ነው

ድሬዳዋ፣ ሐምሌ 10/2018 (ኢዜአ):- የፍርድ ቤት መር አስማሚነት ሥርአት ለህብረተሰቡ ፈጣንና ተደራሽ ፍትህ በመስጠት ማህበራዊ ትስስር እንዲጠናከር እያስቻለ መሆኑ ተገለጸ።

በፌደራል መጀመሪያ ደረጃ  ድሬዳዋ ምድብ ችሎት የፍርድ ቤት መር አስማሚነት ሥርአትን ከዛሬ ጀምሮ ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል የጋራ መግባቢያ ሰነድ ተፈርሟል።

መግባቢያ የሰነዱን የፈረሙት የፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ፉአድ ኪያር እና የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ሀርቢ ቡህ ናቸው።

የፍርድ ቤት መር አስማሚነት ሥርአት አንዳንድ ቤተሰባዊ ጉዳዮችን በማስማማት በፍጥነትና በውጤታማነት ለመጨረስ የሚያስችል የዳኝነት ሥርአት ነው።

የጋራ መግባቢያ ሰነዱም በድሬዳዋ የፍርድ ቤት መር አስማሚነት ማዕከልን በማቋቋም ከባህል ሽማግሌዎች እና ከኃይማኖት ተቋማት አባቶች ጋር በመቀናጀት ለመስራት የሚያስችል መሆኑ ተመላክቷል።

የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ፉአድ ኪያር በስምምነቱ ወቅቱ እንደገለጹት፤ ከአገራዊ ለውጡ በኋላ በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤቶች አዳዲስ ሪፎርሞች እና በቴክኖሊጂ የታገዙ አሰራሮችን በመተግበር ለህብረተሰቡ ፈጣንና ተደራሽ ፍትህ መስጠት ተችሏል።


 

ማህበረሰብ ተኮር ፍትህ እያሰፈኑ ካሉት መካከል በፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤቶች በመተግበር ላይ የሚገኘው የፍርድ ቤት መር አስማሚነት ስርአት አንዱ መሆኑን አንስተዋል።

እንደ ፕሬዚዳንቱ ገለጻ ሥርአቱ አንዳንድ ቤተሰባዊ ጉዳዮችን በማስማማት በፍጥነትና በውጤታማነት በመጨረስ የህዝብ አመኔታን ያተረፈ የዳኝነት ሥርአት ለመገንባት እያገዘ ነው።

ለዚህም በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤቶች በ13 ምድብ ችሎቶች ከውርስ፣ ከቤተሰብ እና መሰል ጉዳዮች ጋር የተያያዙ 1ሺህ 690 መዝገቦችን በስምምነት በመጨረስ ለዜጎች ፈጣንና ቀልጣፋ ፍትህ መስጠት ተችሏል ብለዋል።

በዚህም የማስማማት ጥበብ እና ተቀባይነት ያላቸው የባህልና የኃይማኖት አባቶች የፍርድ ቤት ሥርአትና ነፃነትን ተከትለው የድርሻቸውን እንዲወጡ በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም አስታውቀዋል።

ዛሬ በድሬዳዋ የተፈረመው የሥራ መግባቢያ ሰነድ ተቀባይነትና ዕውቀት ላላቸው የአገር ሽማግሌዎች፣ የኡጋዝ፣ የአባገዳና የእምነት አባቶች ተገቢውን ስልጠና በመስጠት ሥርአቱን ወደ ተግባር የሚያሸጋገር መሆኑን ገልጸዋል። 


 

የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ሀርቢ ቡህ በበኩላቸው፣ የፍርድ ቤት መር አስማሚነት ሥርአት በቤተሰብ፣ በዘመድ አዝማድ እና በነዋሪዎች መካከል የሚነሱ ክርክሮችን በማስማማት ማህበረሰባዊ ትስስርና ግንኙነት በዘላቂነት ለማስቀጠል ያስችላል ብለዋል።

ይህም የፍርድ ቤቶችን ጊዜ በመቆጠብ የመዛግብት ፍሰት ለመቀነስ ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው፣ በዚህ ሥራ የሚሳተፉት ተቀባይነት ያላቸው የባህል አባቶች የህግ ሥርአትን ተከትለው እንደሚሰሩ አመልክተዋል።

የስምምነት ፊርማው ሲፈጸም የአገር ሽማግሌዎች፣ የአባገዳ እና የኡጋዝ ተወካዮች የተሳተፉ ሲሆን ለስምምነቱ  ውጤታማነት ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ቁርጠኛ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

በፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ድሬዳዋ ምድብ ችሎት በፍርድ ቤት መር አስማሚነት ማዕከል የሚከናወኑ ሥራዎች በየሦስት ወራት በተቋቋመ ቴክኒክ ኮሚቴ የሚገመገም መሆኑም ታውቋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም