ቀጥታ፡

የኢትዮጵያን የቆዩ ስብራቶች በመጠገን ወደ አዲስ ምዕራፍ ለማሸጋገር ሀገራዊ ምክክሩ ታሪካዊ እድል ነው

ሀዋሳ፤ሐምሌ 10/2018 (ኢዜአ):-የኢትዮጵያን የቆዩ ስብራቶች በመጠገን ወደ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ለማሸጋገር ሀገራዊ ምክክሩ ታሪካዊ እድል መሆኑን ምሁራን ገለጹ።

በኢትዮጵያ የቆዩ ችግሮችን በዘላቂነት በመፍታት ጠንካራ ሀገረ መንግስት ለመገንባት ሀገራዊ ምክክር ታሪካዊ ዕድል ሆኖ መጥቷል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ተቋቁሞ ከዝግጅት እስከ ምክክር ምዕራፍ በርካታ ውጣ ውረዶችን አልፎ በአሁኑ ወቅት አካታች የሆነ የምክክር ሂደት እያከናወነ ይገኛል።

በኮሚሽኑ የተለዩ አጀንዳዎች ላይ ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ የማጠቃለያ የምክክር ጉባኤ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

አጠቃላይ የምክክር ሂደቱንና ጉባኤውን በተመለከተ ኢዜአ ያነጋገራቸው የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን፤ የኢትዮጵያን የቆዩ ስብራቶች በመጠገን ወደ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ለማሸጋገር ሀገራዊ ምክክሩ ታሪካዊ ዕድል መሆኑን አንስተዋል።

በዩኒቨርሲቲው የስነዜጋና ስነምግባር መምህር ብሩክ ደስታ፤ ሀገራዊ ምክክሩ እንደ ሀገር ትልቅ ተስፋ የሰነቅንበት የጋራ እጣ ፋንታችን ነው ብለዋል።

በመሆኑም ለሀገራዊ ችግሮች ዘላቂ መፍትሔ ለመሻት ለዓመታት የዘለቀው የምክክር ሂደት በውጤታማነት እንዲደመደም የሁላችንም ቅንንት፣መሻትና ለዘላቂ ሰላም መትጋት የግድ ነው ሲሉ አንስተዋል።

ለምክክሩ የተለዩ አጀንዳዎችን በአግባቡ ከተጠቀምንባቸው የኢትዮጵያን ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችሉ አንኳር ጉዳዮች መሆናቸውን ተናግረዋል።

ምክክሩ ሀገራዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ መግባባትን ለመፍጠር ካለው ፋይዳ በተጨማሪ፣ የቆዩ ቁርሾዎችን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመፍታት መፍትሄ ይሆናል ብለዋል።

በዩኒቨርሲቲው ማህበራዊ ሳይንስና ስነሰብ ኮሌጅ መምህርና ተመራማሪ እንዳልካቸው ጀንበሬ (ዶ/ር)፤ በምክክር ችግሮችን የመፍታት ባህልን ማዳበር ዘመኑ የሚጠይቀው ጉዳይና የስልጣኔ መገለጫም ጭምር መሆኑን አንስተዋል።

የሀገር ግንባታ ሂደት የሚሳካው በሰለጠነ ውይይትና ህብረ ብሔራዊ ሀገራዊ አንድነትን በማፅናት መሆኑን ገልጸው፥ታሪካዊ እድል የሆነውን ምክክር ስኬታማ ለማድረግ በሃላፊነት ስሜት መጠቀም ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም