ቀጥታ፡

በዞኑ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎች የተገኘውን ስኬት ለማስቀጠል ይሰራል

ምስራቅ ጎጃም ፤ሐምሌ10/2018(ኢዜአ)፡- በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በልማትና በመልካም አስተዳደር ስራዎች የተገኝውን ስኬት ለማስቀጠል ርብርብ እንደሚደረግ የምስራቅ ጎጃም ዞን አስተዳደር አስታወቀ።

በዞኑ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በልማትና መልካም አስተዳደር  ዘርፎች የነበሩ አፈፃፀሞችን የሚገመግምና የ2019 በጀት  ዓመት እቅድን የሚያስተዋውቅ መድረክ በደብረ ማርቆስ ከተማ ተካሂዷል።


 

የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ዋለ አባተ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎችን በማከናወን ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ መሰራቱን ገልጸዋል።

በተለይ በመኸር ሰብል፣ በመስኖ እና የእንስሳት ሃብት ልማት፣በስራ እድል ፈጠራ፣ በንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ስራዎች የላቀ አፈጻጸም ማስመዝገብ መቻሉን ተናግረዋል።

ከዚሁ ጎን ለጎንም ህብረተሰቡንና የፀጥታ ኃይሉን በማስተባበር ሰላምና ደህንነትን ለማስከበር የተከናወኑት ተግባራት ለውጥ እንዲመዘገብ አያደረጉ መሆኑን አስረድተዋል።

በአሁኑ ወቅትም የሚስተዋሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመቅረፍም በየተቋማቱ በዲጅታል ቴክኖሎጀ የታገዘ ቀልጣፋ፣ ተጠያቂነት ያለውና ፍትሃዊ አገልግሎት ለመስጠት ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በበጀት ዓመቱ የታዩ ክፍተቶችን ለማረምና  ጠንካራ ጎኖችን ደግሞ ይበልጥ አጠናክሮ በማስቀጠል ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ በመታቀዱ የውይይት መድረኩ መዘጋጀቱን ገልፀዋል።

የዞኑ ግብርና መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ ጥላሁን ንጋቱ በበኩላቸው፤ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የአርሶ አደሩንና የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ርብርብ መደረጉን አብራርተዋል።

በዚሁ ወቅት በመኸር ሰብል ልማት ከ21 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት በማምረት ከእቅድ በላይ አፈፃፀም ለማስመዝገብ መቻሉን አስረድተዋል።

የመንገድ ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ መምሪያ ኃላፊ አቶ ማናየ አዳነ በበኩላቸው ፤በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በዘርፉ ስኬታማ ስራዎችን ለማከናወን መቻሉን ነው የተናገሩት።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም