ቀጥታ፡

የምግብ ሉዓላዊነትን የማረጋገጥ ጉዳይ ቀጣይነት ያለው አጀንዳችን ነው- ምክትል ፕሬዚዳንት አወሉ አብዲ

አዳማ፤ ሐምሌ 10/2018(ኢዜአ )፡-የግብርና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ሉዓላዊነትን የማረጋገጥ ጉዳይ ቀጣይነት ያለው አጀንዳችን ነው ሲሉ የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዘዳንት አወሉ አብዲ ገለጹ።

3ኛው የኦሮሚያ ቡሳ ጎኖፋ ጠቅላላ ጉባኤ በአዳማ ገልመ አባገዳ አዳራሽ ዛሬ ተካሄዷል።


 

የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት አወሉ አብዲ በወቅቱ እንደገለፁት በክልሉ የግብርና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ትኩረት ተሰጥቷል።

ይህም ለሰው ሰራሽና ለተፈጥሮ አደጋዎች በራስ አቅም ፈጣን ምላሽ ለመስጠትና የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ድርሻው የጎላ መሆኑን አስረድተዋል። 

ለተግባራዊነቱም ከኦሮሞ ሕዝብ የመረዳዳት ባህል የተቀዳውን ቡሳ ጎኖፋ ሥራ ላይ በማዋል ውጤት መገኘቱን ጠቁመዋል።

ቡሳ ጎኖፋ የማኅበረሰቡን የመረዳዳት ባህል ይበልጥ ለማጎልበትና በምግብ ራስን ለመቻል ተደማሪ  አቅም መሆኑን ጠቅሰዋል።


 

ይህም በክልሉ ዝናብ አጠር በሆኑ 59 ወረዳዎች ሊከሰቱ የሚችሉ ማህበራዊ ችግሮችን መቋቋም የሚያስችል ዝግጅት ለማድረግ ማገዙን ተናግረዋል።

ተግባሩ ለሰዎች የሚሆን የምግብ ክምችትን ከማሳደግ ባለፈ ውሃን በማቆር የእንስሳት መኖ ለማልማት ማስቻሉን ጠቅሰዋል።

የቡሳ ጎኖፋ የጠቅላላ ጉባኤ ሰብሳቢ አምባሳደር አለማየሁ ተገኑ በበኩላቸው ቡሳ ጎኖፋ በክልሉ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎችን በራስ አቅም  ለመቋቋም እያገዘ ነው ብለዋል።


 

ለዚህም በእርሻ ሥራና በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ እየተሰማራ ይገኛል ያሉት አምባሳደር አለማየሁ፣ ለዚህም በቡልቡላና በነቀምቴ  ከተሞች የተቀናጀ የማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪዎች እየገነባ ነው ብለዋል።

በአዲሱ በጀት ዓመት  ይህንን በቅንጅት  ለማሳካት  መረባረብ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

የኦሮሚያ ቡሳ ጎኖፋ ሃላፊ አቶ ሙሐመድ ጁንዳ እንደገለፁት በክልሉ እስካሁን ድረስ 29 ነጥብ 4 ሚሊዮን አባላት ማፍራት መቻሉን አንስተዋል።

በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ከ3 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት ሀብት በማሰባሰብ ለአቅመ ደካማ ወገኖች ድጋፍ መደረጉን ጠቁመዋል።


 

በአይነት ከተሰበሰበው ከ2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኩንታል በላይ እህልም  ለተማሪዎች ምገባና ለመጠባበቂያነት መዋሉን  ገልጸዋል። 

ተግባሩን ለማሳካትም  በእርሻ፣ በእንስሳት እርባታና በመጋዘን ግንባታዎች ላይ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም