ቀጥታ፡

ታላቁ የሕዳሴ ግድብ የቅኝ ግዛት ዘመን የተሳሳተ ትርክትን የሰበረ የፍትሐዊነትና የምክንያታዊነት አህጉራዊ ምልክት ነው - ፕሮፌሰር ዓለማየሁ ገብረማርያም

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 10/2018(ኢዜአ)፦ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ድንበር ተሻጋሪ የውሃ ሀብቶችን በብቸኝነት የመጠቀም የቅኝ ግዛት ዘመን የተሳሳተ ትርክት የሰበረ የፍትሐዊነትና ምክንያታዊነት አህጉራዊ ምልክት መሆኑን በካሊፎርኒያ ስቴት ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና የሕግ ባለሙያው ፕሮፌሰር ዓለማየሁ ገብረማርያም ገለጹ።

ፕሮፌሰር ዓለማየሁ ገብረማርያም ለኢዜአ እንዳሉት፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መገንባት የቀጣናው ሀገራት የኢኮኖሚ ዕድገትን በማፋጠን ለጋራ ተጠቃሚነት ትልቅ በረከት ከፍቷል።

የታችኛው የዓባይ ተፋሰስ ሀገራትም  ላይም ሊደስር የሚችለውን የጎርፍ መጥለቅለቅና የውሃ ብክነትን በመቀነስ የተመጣጠነ የውሃ ፍሰት እንዲያገኙ እያስቻለ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የታላቁ ሕዳሴ ግድብን እውን በማድረግ በድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ፍትሐዊ የውሃ ሃብት አጠቃቀም ላይ አዲስ የጋራ ተጠቃሚነት መርህን ማብሰር እንደቻለች ተናግረዋል።


 

ነገር ግን ግብፅ አሁንም ድረስ በዓባይ ወንዝ ላይ ለዘመናት የነበራትን የቅኝ ግዛትና ታሪካዊ በብቸኝነት የመቆጣጠር አባዜ ዛሬም ድረስ እያስተጋባች እንደሚገኝ አስረድተዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በዓባይ ወንዝ ላይ የነበረውን የቅኝ ግዛት ዘመን የተሳሳተ ትርክት በመስበር የጋራ ተጠቃሚነትን ያበሰረ ግዙፍ አፍሪካዊ ፕሮጀክት መሆኑን አንስተዋል።

የታላቁ ሕዳሴ ግድብ የዓባይን ውሃ በብቸኝነት የመጠቀምን የቀድሞ የተሳሳተ አመለካከት መስበሩን የገለጹት ፕሮፌሰር ዓለማየሁ፤ አዲስ የድንበር ተሻጋሪ የውሃ ሃብትን በፍትሐዊና ምክንያታዊነት የመጠቀም አህጉራዊ ምልክት ሆኗል ብለዋል።

ግብፅ የቅኝ ግዛት ውሎችን በመጠቀም ለዘመናት የዓባይን ውሃ በብቸኝነት ስትጠቀም መቆየቷን በማስታወስ፤ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ላይ የምታቀርባቸው የተሳሳቱ መረጃዎች መሰረተ ቢስ ክስ መሆኑን ገልጸዋል።

እ.ኤ.አ የ1891 የእንግሊዝ ጣሊያን ፕሮቶኮል፣ እ.ኤ.አ የ1906 የብሪታንያ፣ ፈረንሳይና ጣሊያን የሶስትዮሽ፣ እ.ኤ.አ የ1929 የእንግሊዝ ግብፅ እና እ.ኤ.አ በ1959 የግብፅ ሱዳን የተደረጉ ስምምነቶች የዓባይ ምንጭ የሆነችውን ኢትዮጵያ ያገለሉ እንደነበር አስታውሰዋል።

የታሪክ ማስረጃን በማጣቀስ በእርግጥ በብቸኝነት የተንቀሳቀሰው ማን ነው? ሲሉ የጠየቁት ፕሮፌሰሩ፤ ኢትዮጵያን ከመክሰስ ይልቅ ከዚህ በፊት የነበሩ ስሁት ትርክቶችን ወደኋላ መመልከት ተገቢ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ በሁለትዮሽና ባለብዙ ወገን የዲፕሎማሲ ትብብር መርህ መሆኑን በቀጣናዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ መድረክ እያስመሰከረች መሆኑን አንስተዋል።

የታላቁ ሕዳሴ ግድብም የትብብር እንጂ በብቸኝነት የመጠቀም ፕሮጀክት አይደለም ያሉት ፕሮፌሰር ዓለማየሁ፤ ለዚህም ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ በ2015 ከግብፅና ሱዳን ጋር የፈረመችውን የሕዳሴ ግድብ መርህ ለማክበር በተደጋጋሚ ቃል ገብታለች  ብለዋል።

የናይል ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነትን የፈረሙት ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ሩዋንዳ፣ ታንዛኒያ፣ ቡሩንዲና ደቡብ ሱዳንም በዓባይ ወንዝ ላይ የቅኝ ግዛት ዘመን አድሏዊ ስምምነቶችን የሻረ መሆኑን አብራርተዋል።

እ.ኤ.አ ከ2024 ጥቅምት 13 ጀምሮ በሥራ ላይ የዋለው ማዕቀፍም ፍትሐዊና ምክንያታዊ የውሃ ሃብት አጠቃቀም ሕግ ቢሆንም፤ ግብፅና ሱዳንም ስምምነቱን በመፈረም ትብብርን ሊያጎለብቱ እንደሚገባ አስገንዝዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኖቤል የሰላም ሽልማት ላይ ባደረጉት ንግግር የአፍሪካ ቀንድ የኃያላን መፎካከሪያና የአሸባሪዎች መሸሸጊያ ሳይሆን የሰላም፣ የትብብርና የብልፅግና ቀጣና እንዲሆን ያላቸውን ርዕይ መግለፃቸውን አስታውሰዋል።

በሌላ መልኩም እ.ኤ.አ በ2018 በካይሮ ለግብፅ ሕዝብ ኢትዮጵያ የግብፅን የውሃ ጥቅም አትጎዳም በማለት በገቡት ቃል መሰረት የታላቁ ሕዳሴ ግድብ በዓባይ የውሃ ፍስት ላይ አንዳችም ጉዳት እንዳላደረሰ አስረድተዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የጭቅጭቅ መንስኤ ሳይሆን፣ የምስራቅ አፍሪካ የኢኮኖሚ ትስስር፣ የኃይል ትብብርና የጋራ ብልፅግና ማሳለጫ የአፍሪካ ተስፋ መሆኑን አስገንዝበዋል።

በተጨማሪም የታላቁ ሕዳሴ ግድብ የአፍሪካ ቀንድና ለመላው አፍሪካ የጋራ ዕድገት ግዙፍ ምልክት ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም