በማረሚያ ቤቶች የሚሰጠውን የጤና አገልግሎት ተደራሽነትና ጥራት ይበልጥ አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
በማረሚያ ቤቶች የሚሰጠውን የጤና አገልግሎት ተደራሽነትና ጥራት ይበልጥ አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 10/2018(ኢዜአ)፦ በማረሚያ ቤቶች የሚሰጠውን የጤና አገልግሎት ተደራሽነትና ጥራት ይበልጥ አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል ሲሉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባዔ ሎሚ በዶ ገለጹ።
የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ በበኩላቸው፥ በማረሚያ ቤቶች የሚሰጠውን የጤና አገልግሎት በቋሚ የጤና ሥርዓት ውስጥ በማካተት፣ ተደራሽነቱንና ጥራቱን ለማሻሻል የተቀናጀ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
የ2018 ዓ.ም የጤና ዘርፍ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት መርሐ ግብር በሸገር ከተማ ዳለቲ ማረሚያ ቤት በይፋ ተጀምሯል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባዔ ሎሚ በዶ በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግር፥ ማረሚያ ቤቶች የሕግ የበላይነት የሚከበርባቸው ስፍራዎች ብቻ ሳይሆኑ፣ ሰብዓዊነት የሚነግስባቸውና ታራሚዎች በዕውቀት፣ በክህሎትና በሥነ-ልቦና ታንጸው ወደ ማኅበረሰቡ የሚቀላቀሉባቸው የለውጥ ማዕከላት ናቸው ብለዋል።
ታራሚዎች እንደማንኛውም ዜጋ ማግኘት ያለባቸውን ሰብዓዊና የጤና ክብካቤ ሁሉ የማግኘት መብት አላቸው ያሉ ሲሆን የሚያገኙትን የሕክምና አገልግሎት ተደራሽነትና ጥራት ይበልጥ ማሳደግ እንደሚገባ ተናግረዋል።
የክረምት በጎ ፈቃድ የጤና አገልግሎትም ለህክምና ተደራሽነት የራሱ አጋዥ ሚና እንዳለው ጠቅሰው፥ በማረሚያ ቤቶች የሚሰጠውን የጤና አገልግሎት ይበልጥ ማስፋት ያስፈልጋል ነው ያሉት።
የመንግሥትና የግል የጤና ባለሙያዎችን በማስተባበር በየወቅቱ ሰፋ ያለ የሕክምናና የምርመራ ተግባርን ማከናወን እንደሚገባ አመላክተዋል።
የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ፤ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት የተጀመረ ሀገራዊ ንቅናቄ ሲሆን፣ ሚኒስቴሩም ይህንን ተሞክሮ በጤናው ዘርፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
በጤና ዘርፉ በየዓመቱ የሚካሄደው የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት በሀገር ውስጥ ከሚገኙ የጤና ባለሙያዎች በተጨማሪ፣ በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ዳያስፖራ የጤና ባለሙያዎችንና ሌሎች በጎ ፈቃደኞችን በማሳተፍ እየተከናወነ ነው ብለዋል።
ይህም ለበርካታ ዜጎች ተደራሽ የጤና አገልግሎትን ለማስፋት ዕድል እየፈጠረ መሆኑን አመልክተዋል።
በማረሚያ ቤቶች የሚገኙ ታራሚዎችም ነጻ፣ ጥራት ያለውና ፍትሐዊ የጤና አገልግሎት እንዲያገኙ እያስቻለ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በማረሚያ ቤቶቹ ያሉ የጤና ተቋማት አቅም እንዲጠናከርና የአገልግሎት ደረጃቸው እንዲሻሻል የሚያስችሉ ሥራዎች እንደሚከናወኑ አስረድተዋል።
መርሐ ግብሩ የአንድ ቀን ወይም የአንድ ጊዜ እንቅስቃሴ ሳይሆን፣ በመላ ሀገሪቱ በሚገኙ የጤና ተቋማትና ማረሚያ ቤቶች በቀጣይነት የሚተገበር ዘላቂ ፕሮግራም መሆኑንም አብራርተዋል።
በመርሐ ግብሩ የተሳተፉ አመራሮችና ባለድርሻ አካላት የአረንጓዴ ዐሻራ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር አከናውነዋል።