ቀጥታ፡

በሰሜን ሸዋ ዞን ከ199 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የጠጠር መንገዶች ተገንብተዋል

ደብረ ብርሃን ፤ ሐምሌ 10/2018(ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በ199 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ 72  ኪሎ ሜትር የጠጠር መንገድ መገንባቱን የዞኑ መንገድ ትራንስፖርትና ሎጅስቲክ  መምሪያ ገለጸ።

የመምሪያው ኃላፊ አቶ ደጀኔ በቀለ ለኢዜአ እንደገለጹት፤የተገነቡት አዲስ የጠጠር መንገዶች  የመንገድ ተደራሽነት ባልነበረባቸው 11 ወረዳዎች በሚገኙ ቀበሌዎች ውስጥ ነው፡፡

የመንገድ ግንባታው በአገረ ማሪያም ከሰም ወረዳ  ቅዱስጌ ከሰም፤በመርሐቤቴ ወረዳ ከዋና መንገድ ሐና ቤተክርስቲያን፤  በሞረትና ጅሩ ዲላሞ ቀበሌን ጨምሮ 11  ወረዳዎች  መካሔዱን ጠቅሰዋል፡፡


 

የተገነቡት መንገዶች ክረምት  ከበጋ 42 ሺህ ለሚደርሱ የአካባቢው ነዋሪዎች አገልግሎት መስጠት የሚችሉ መሆኑን ገልፀዋል።

የመንገዶቹ  መገንባት በዞኑ  3 ሺህ 346 ኪሎሜትር የነበረውን ሽፋን ወደ 3 ሺህ 421 ኪሎሜትር የሚያሳድግ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በበጀት ዓመቱ ከመንገድ ግንባታው ጎን ለጎን  የተለያዩ የድልድይ ግንባታ ስራዎች መከናወናቸውን ነው አቶ ደጀኔ  የገለጹት።

ለመንገድ ግንባታው ወጪ የተደረገው ከ199 ሚሊየን ብር  በላይ የሚሆን ገንዘብ በክልሉ መንግስት የተሸፈነ ሲሆን የማሕበረሰቡ ተሳትፎም ከፍተኛ እንደነበር  ገልፀዋል።


 

በመንገድ ዘርፍ በበጀት ዓመቱ ለ7 ሺህ 522 ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ ዕድል መፈጠሩንም አክለው አብራርተዋል፡፡

የተገነቡት መንገዶች የአርሶ አደሩን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስር ለማጠናከር የጎላ ድርሻ እንዳላቸው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም