ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የዲጂታል እመርታ የትምህርት ጥራትና ተደራሽነትን በማሳለጥ ውጤታማነት እያሳደገ ነው

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 10/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የዲጂታል እመርታ የትምህርት ጥራትና ተደራሽነትን በማሳለጥ ውጤታማነት እያሳደገ መሆኑን የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ አየለች እሸቴ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በ30ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽ እና ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት፣ በሀገሪቱ በትምህርት ዘርፍ የተመዘገበው ስኬት እጅግ የሚያኮራ እና ተስፋ ሰጪ መሆኑን ገልጸዋል።

መንግሥት ከታችኛው የትምህርት እርከን ጀምሮ ለጥራት፣ ለቴክኖሎጂ አጠቃቀምና የፈተና ስርቆትን ለመከላከል የሰጠው ትኩረት ዘርፉን በአዲስ ምዕራፍ ላይ ለማስቀመጥ የላቀ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል።

ይህ የተቀናጀ ጥረት የትምህርት ጥራትን አስተማማኝ መሰረት ላይ ለመጣልና የትውልዱን ብቃት ለማሳደግ በሚደረገው ጉዞ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አረጋግጠዋል።

የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ አየለች እሸቴ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ መንግሥት በትምህርት ዘርፉ የሚስተዋሉ ስብራቶችን ለመጠገንና ጥራትን ለማረጋገጥ በለውጡ ዓመታት መጠነ ሰፊ የሪፎርም ሥራዎችን አከናውኗል።

በዚህም የትምህርት ተደራሽነትንና ጥራትን በዘላቂነት ማረጋገጥ የሚያስችሉ በርካታ ስትራቴጂዎችን በመንደፍ ተግባራዊ መደረጋቸውን ገልጸዋል።

ተማሪዎችን በቴክኖሎጂ፣ በእውቀትና በክህሎት ለማብቃት ከዋና ዋና ከተሞች እስከ ገጠር ትምህርት ቤቶች የኮምፒውተር ላብራቶሪዎችን የማደራጀትና የማስፋፋት ሥራ መከናወኑን ተናግረዋል።

አጠቃላይ የትምህርት ሥርዓቱን በቴክኖሎጂ የታገዘ ለማድረግ በተከናወኑ ተግባራት አበረታች ውጤቶች ተመዝግበዋል ነው ያሉት።

ዘመኑ የሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) እንደመሆኑ መጠን ይህንን ቴክኖሎጂ ከመማር ማስተማር ሂደቱ ጋር ማጣመር የትምህርት ጥራትንና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም ሥርዓቱን በሰው ሰራሽ አስተውሎት ለመደገፍ ሰፊ የዝግጅት ሥራዎች መከናወናቸውን አንስተዋል።

ይህ የቴክኖሎጂ ሽግግር የመምህራንን የሥራ ጫና በከፍተኛ ሁኔታ የሚቀንስ ከመሆኑም በላይ፣ የተማሪዎችንና የመምህራንን ጊዜ በመቆጠብ የትምህርት ጥራትን በዘላቂነት ለማረጋገጥ የላቀ ፋይዳ እንደሚኖረው አስረድተዋል።

በተጨማሪም፣ ይህ የፈጠራ ሽግግር የክፍል ውስጥ ትምህርትን ይበልጥ ሳቢና ቀልጣፋ ከማድረጉ በላይ፣ መምህራን በክህሎት የበለጸገ እና ለቴክኖሎጂው ዓለም ዝግጁ የሆነ ትውልድ እንዲያፈሩ ያስችላቸዋል ነው ያሉት።

ቴክኖሎጂ በትምህርት ዘርፍ ላቅ ያለ ሚና ያለው በመሆኑ፣ ሀገራዊ ተደራሽነቱን ለማስፋት በትኩረት እየተሠራ መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታዋ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም