ቀጥታ፡

በሲዳማ ክልል ህብረተሰቡን ያሳተፈ የወባ በሽታ መከላከል ሥራ እየተከናወነ ነው 

ሀዋሳ፤ ሐምሌ 10/2018(ኢዜአ)፦ በሲዳማ ክልል ህብረተሰቡን ያሳተፈ የወባ በሽታ መከላከል ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ፡፡

የቢሮው ምክትልና በሽታ መከላከልና ጤና ማጎልበት ዘርፍ ሃላፊ አቶ በላይነህ በቀለ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የክረምት ወራት መግባትን ተከትሎ ሊከሰት የሚችለውን የወባ ስርጭት ለመከላከልና ለመቆጣጠር ህብረተሰቡን ያሳተፍ ሥራ እየተሰራ ነው።

በዚህም የማህበረሰቡን ግንዛቤ በማሳደግ የግልና የአካባቢ ንጽህና መጠበቅ ላይ በትኩረት መሰራቱን  ነው የገለጹት፡፡

በዋናነትም ህብረተሰቡን በማንቀሳቀስ ለወባ መራቢያ ምቹ የሆኑ ውሃ ያቆሩ ስፍራዎችን የማዳፈን፣ የማፋሰስና ቆሻሻ ቦታዎችን የማጽዳት ሥራ እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

በክልሉ የወባ ስርጭት ባለባቸው አራት ወረዳዎች ቤት ለቤት የጸረ ወባ ኬሚካል ርጭት መደረጉንና ከ850 ሺህ በላይ የአልጋ አጎበር መሰራጨቱንም ተናግረዋል፡፡

ከወባ መከላከል ስራው በተጨማሪ በበሽታው የተያዙ ሕሙማን አፋጠኝ ሕክምና እንዲያገኙ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ጤና መምሪያ በሽታ መከላከል ዳይሬክቶሬት የወባ መከላከልና መቆጣጠር ኦፊሰር አቶ ዮናስ ለማ በበኩላቸው እንዳሉት፤ የወባ በሽታ ስርጭትን ለመከላከል በሚከናወኑ ስራዎች የህብረተሰቡ ተሳትፎ እያደገ መጥቷል፡፡


 

በዚህም ውሃ ያቆሩ ቦታዎችን በማዳፈንና በማፋሰስ ወባን የመከላከል ስራ መሰራቱን ገልጸዋል።

ህብረተሰቡ የአልጋ አጎበሮችን በአግባቡ በመጠቀም ወባን እንዲከላከል መደረጉን ገልጸው፣ በቱላ ክፍለ ከተማ በሚገኙ 12 ቀበሌዎች የቤት ለቤት የጸረ ወባ ኬሚካል ርጭት ተጀምሯል ብለዋል።

በሀዋሳ ከተማ ቱላ ክፍለ ከተማ ነዋሪዎችም አካባቢያቸውን ከወባ በሽታ ተጋላጭነት ለመከላከል የሚያስችል ሙያዊ ድጋፍ ከጤና ባለሙያዎች ማግኘታቸውን ጠቅሰዋል።


 

በተፈጠረላቸው ግንዛቤም በአካባቢያቸው ውሃ ያቆሩ ቦታዎችን የማዳፈንና የማፋሰስ ሥራ ከማከናወን ባለፈ በመኖሪያ ቤታቸው የጸረ ወባ ኬሚካል ርጭት እንዲሁም የቤተሰባቸው የአልጋ አጎበር አጠቃቀምን ማስተካከላቸውንም ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም