ቀጥታ፡

ሀገራዊ ለውጡ የፈጠረው አሳታፊ የፖለቲካ ምህዳር ለሰለጠነ የፖለቲካ ባህል መሰረት ጥሏል

ሆሳዕና፤ ሐምሌ 10/2018(ኢዜአ)፦ ሀገራዊ ለውጡ የፈጠረው አሳታፊ የፖለቲካ ምህዳር የፖለቲካ ፓርቲዎች በሰላምና በልማት ጉዳዮች ላይ ተቀራርበው የመስራት ባህል እንዲያዳብሩ ማድረጉን የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገለጹ።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የዩኒቨርሲቲ መምህራንና ተመራማሪዎች እንዳሉት፤ ሀገራዊ ለውጡ የፈጠረው አሳታፊ ስርአት በህዝብ ይሁንታ የተመሰረተ መንግስት በማዋቀር ዴሞክራሲያዊ መንግስት ለመመስረት ይረዳል። 

ሂደቱም የበለጸገችና የተረጋጋች ሀገርን ለተተኪ ትውልድ ለማስተላለፍ ጠንካራ መሰረት እንደሚሆን አስገንዝበዋል።

በዩኒቨርሲቲው የፖለቲካ ሳይንስ መምህር ዳንኤል ሀንዲኖ (ዶ/ር)  እንደገለጹት፤ ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ የተፈጠረው  አሳታፊ የፖለቲካ ሥርዓት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሀሳብ ልዩነቶቻቸው እንደተጠበቀ ሆኖ ለሀገር ሰላምና ልማት ተቀራርቦ መስራታቸው እንዲጠናከር አድርጓል።

ይህም ለዴሞክራሲያዊ ሥርአት ዕድገት ከሚኖረው አስተዋጽኦ በተጨማሪ ከመፈራረጅና ከቂም በቀል ዕሳቤ ወጥተው ለትብብርና ለሰለጠነ የፖለቲካ እንቅስቃሴ አዲስ ምዕራፍ ከፍቷል።

የዴሞክራሲ ተቋማት አሰራር እና የህግ ማዕቀፎችን በማሻሻል ተአማኒ፣ ጠንካራና የማስፈጸም እቅማቸው እንዲጨምር መደረጉ ውጤት እያመጣ መሆኑንም ተናግረዋል።

በዩኒቨርሲቲው የሰላምና ግጭት ጥናት መምህር ጌታሁን አበራ በበኩላቸው፤ የለውጡ መንግስት የመድበለ ፓርቲ ስርአትን በማስፋት ፓርቲዎች በሀገራዊ ጉዳዮች ተቀራርብው የሚሰሩበትን አውድ መፍጠሩን ተናግረዋል። 

ለዚህም ተፎካካሪ ፓርቲዎች በመንግስት ከፍተኛ የሀላፊነት ቦታ ላይ ጭምር በቅንጅት በመስራት እያከናወኑት ያለው ተግባር በምሳሌነት የሚጠቀስ መሆኑን ገልጸዋል።

በሀገረ መንግስት ግንባታ ሂደት ሚናቸውን እንዲያጠናክሩ መንግስት ምቹ ምህዳር ከመፍጠር ባለፈ የተቋማትን የመፈጸም አቅም በማጠናከር የተገልጋይን እርካታ ለማሳደግ መሰራቱን አንስተዋል።

በተለይ ዴሞክራሲያዊ ተቋማት መጠናከራቸው  ዴሞክራሲን በማጠናከር የበለፀገች ሀገርን ለትውልድ ለማስተላለፍ ያስችላል ብለዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም