የሀረሪ ክልል ምክር ቤት መደበኛ ጉባዔ ረቂቅ አዋጆችን እና ሹመቶችን በማፅደቅ ተጠናቀቀ - ኢዜአ አማርኛ
የሀረሪ ክልል ምክር ቤት መደበኛ ጉባዔ ረቂቅ አዋጆችን እና ሹመቶችን በማፅደቅ ተጠናቀቀ
ሀረር፤ ሐምሌ 10/2018(ኢዜአ)፦ የሐረሪ ክልል ምክር ቤት ስድስተኛ ዙር አምስተኛ ዓመት አስረኛ መደበኛ ጉባዔ ረቂቅ አዋጆች እና ሹመቶችን በማፅደቅ ተጠናቀቀ።
ምክር ቤቱ ባካሄደው መደበኛ ጉባዔ የሀረሪ ብዙኃን መገናኛ ኤጀንሲን የሀረሪ ብሮድካስቲንግ ኔትዎርክ በሚል ስያሜ እንደገና ለማቋቋም የወጣ ረቂቅ አዋጅን አጽድቋል።
ማሻሻያ አዋጁ ተቋሙ ከዚህ ቀደም ይጠራበት የነበረውን የሀረሪ ብዙሃን መገናኝ ኤጀንሲ ስያሜ ከመቀየር ጀምሮ ለውጥ የተደረገበት ነው።
የተቋሙን ሥልጣንና ተግባራት የሕዝብ ብሮድካስት አገልግሎት ተቋማት በአሁኑ ወቅት ከደረሱበት የዕድገት ደረጃ ጋር እንዲጣጣም በማድረግ በብቃት፣ በጥራትና ውጤታማ እንዲሆን ለማስቻል በብሮድካስቲንግ ኔትዎርክ ደረጃ ማቋቋም አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ማሻሻያ ማድረጉ እንዳስፈለገ ተገልጿል።
አዋጁ ከጸደቀበት ከዛሬ ጀምሮ የሀረሪ ብሮድካስቲንግ ኔትወርክ ተጠሪነቱ ለክልሉ ምክር ቤት እንደሚሆን በአዋጁ ተቀምጧል።
ምክር ቤቱ የቀረበለትን የአስተዳደር ስነ ስርዓት አዋጅም አጽድቋል፡፡
አዋጁም ዜጎች መብትና ግዴታቸውን ተረድተው የሚያጋጥሟቸውን የመልካም አስተዳደር ችግሮች ተገቢ ምላሽ እንዲያገኙ ለማድረግ የሚያስችል መሆኑ ተገልጿል።
እንዲሁም ምክር ቤቱ የሶስት ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞች ሹመትም አጽድቋል።
ምክር ቤቱም ለሁለት ቀናት ያካሄደውን ስድስተኛ ዙር አምስተኛ ዓመት አስረኛ መደበኛ ጉባዔ አጠናቋል።