በክልሉ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎችን በራስ አቅም ለመከላከልና ምላሽ ለመስጠት ዝግጅት እየተደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎችን በራስ አቅም ለመከላከልና ምላሽ ለመስጠት ዝግጅት እየተደረገ ነው
ቦንጋ፤ ሐምሌ 10/2018(ኢዜአ)፦በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎችን ቀድሞ ለመከላከልና ሲከሰትም በራስ አቅም ምላሽ ለመስጠት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የክልሉ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ገለጸ።
ከተረጂነት በመላቀቅ ለሚከሰቱ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች በራስ አቅም ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ትኩረት ተሰጥቶ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑም ተመላክቷል።
የክልሉ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር ለማ መሠለ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለጹት፣ በክልሉ ሊከሰቱ የሚችሉ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎችን በራስ አቅም ምላሽ ለመስጠት የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ነው::
በክልሉ ቆላማ አካባቢዎች በተከሰተ የዝናብ እጥረት እና እርጥበት በበልግ ወቅት በ30 ሺህ ሄክታር ማሳ የለማ ሰብል ላይ ጉዳት ማድረሱን አስታውሰዋል።
በዚህም በቀጣይ በእነዚህ አካባቢዎች ሊፈጠር የሚችለውን የምግብ እጥረት ችግር ለመፍታት በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚደርሱ የሰብል እና የተለያዩ ሥራስሮችን የማልማት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
በሌሎች የክልሉ አካባቢዎች መደበኛ ዝናብ ቀድሞ እንደሚጀምርና ከመደበኛ በላይ ዝናብ ሊኖር እንደሚችል ከአየር ትንበያ የተገኘ መረጃ ያሳያል ያሉት ኮሚሽነር ለማ (ዶ/ር)፤ ይህም ጎርፍ፣ የመሬት ናዳና ሌሎች አደጋዎችን ሊያስከትል እንደሚችል አመልክተዋል።
በዚህ ሊከሰት የሚችልን ድንገተኛ አደጋ ቀድሞ ለመከላከል በስጋት በተለዩ 573 ቦታዎች ላይ የህብረተሰቡን ግንዛቤ ከማሳደግ ባለፈ የቅደመ መከላከል ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በተጨማሪም በዝናብ እጥረትም ሆነ ከመደበኛ በላይ በሆነ ዝናብ ለሚከሰት አደጋ በራስ አቅም ፈጣን ምላሽ ለመስጠት በየደረጃው ጠንካራ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ኮሚሽነሩ ገልፀዋል ።
ለዚህም ከክልል ጀምሮ እስከ ቀበሌ ድረስ የእህል ክምችት፣ የመጠባበቂያ ፈንድ፣ የቤት ውስጥ ቁሳቁስ የማሰባሰብና ሌሎች ተግባራት ተጠናክረው መቀጠላቸውን ነው ያነሱት።
እስካሁንም 800 ኩንታል የሕፃናት አልሚ ምግብ፣ ከ7ሺህ 200 በላይ ኩንታል የእህል ክምችት፣ 1ሺህ 474 ቁሳቁስ እና ሌሎች አስፈላጊ ዝግጅቶች መደረጋቸውን ኮሚሽነሩ አስረድተዋል።
ዝግጅቱ በየደረጃው ተጠናክሮ መቀጠሉን ጠቅሰው፣ የከፋ ችግር ካጋጠመም ከተረጂነት ወጥቶ በራስ አቅም ምላሽ ለመስጠት ከ48 ሚሊዮን ብር በላይ መጠባበቂያ ፈንድ ተይዟል ብለዋል።
ህብረተሰቡ የተፈጠረለትን ግንዛቤ በአግባቡ በመተግበር ራሱን ሊከሰቱ ከሚችሉ አደጋዎች መከላከል እንዳለበትና ባለድርሻ አካላትም ጠንካራ ክትትል ማድረግ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።