የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የ2018 በጀት ዓመት ማጠቃለያ ስራዎች አፈፃፀም ግምገማ ማካሄድ ጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የ2018 በጀት ዓመት ማጠቃለያ ስራዎች አፈፃፀም ግምገማ ማካሄድ ጀመረ
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 10/2018(ኢዜአ)፦ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የ2018 በጀት ዓመት ማጠቃለያ ስራዎች አፈፃፀም ግምገማ ማካሄድ ጀምሯል።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት ዛሬ የከተማ አስተዳደራችንን የ2018 በጀት ዓመት ማጠቃለያ ስራዎች አፈፃፀም ግምገማ ማካሄድ ጀምረናል ብለዋል።
ለሶስት ተከታታይ ቀናት በሚቆየው የአፈፃፀም ግምገማ መድረክ በበጀት ዓመቱ ለመፈፀም ያስቀመጥናቸውን ግቦች፣ እንዲሁም የ2018 በጀት ዓመት የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ እቅዳችን ማጠቃለያ ዓመትም በመሆኑ ከባለፉት 5 ዓመታት አፈፃፀም ጋር አያይዘን የምንገመግም ይሆናል ነው ያሉት።
እንደሚታወቀው ባለፉት 5 ዓመታት ያቀድናቸውን ስትራቴጂክ ግቦች በተሟላ ሁኔታ ለመተግበር በታማኝነትና በቅንነት ያለ እረፍት 24/7 ሰርተን በርካታ ውጤቶችን አስመዝግበናል ሲሉም ገልጸዋል።
በተለይም መዲናችንን አዲስ አበባን ከማይጠቅሙ አጀንዳዎች አውጥተን የልማት እና የሰላም ማዕከል እንድትሆን አድርገናታል ብለዋል።
እንዲሁም ማህበራዊ ፍትህ የነገሰባት፣ ፅዱ፣ አረንጓዴና ውብ እየሆነች በመምጣቷ የዓለምን ትኩረትን ስባለች ሲሉ ጠቁመዋል።
በእርግጥ ከስኬቶቻችን ባሻገር ዛሬም ያልተሻገርናቸው ተግዳሮቶች አሉብን። በተለይ የአመራራችን የውጤታማነት ልዩነቶች፣ በከተማችን የሚታዩ የኑሮ ውድነት እና ፍልሰት ችግሮችን በጥልቀት የምንገመግም ይሆናል ነው ያሉት።
በርካታ ስኬቶችን ብናስመዘግብም ከህዝቡ የመልማት ፍላጎት እና ከብልፅግና ግባችን አንፃር ብዙ ስለሚቀረን ስኬቶቻችንን ማስፋት፤ ተግዳሮቶች ደግሞ ለይተን መፍታት በቀጣይ በጀት ዓመት የላቀ ስኬት ማስመዝገብ የግምገማችን ማዕከል ይሆናል ብለዋል።
በቀጣይ ትኩረት አቅጣጫዎችም ላይ እንወያያለን ሲሉም በመልዕክታቸው አስታውቀዋል።