በምዕራብ ሐረርጌ ዞን በለውዝ ልማት የተሰማሩ አርሶ አደሮች ኑሯቸው እየተሻሻለ መምጣቱን ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
በምዕራብ ሐረርጌ ዞን በለውዝ ልማት የተሰማሩ አርሶ አደሮች ኑሯቸው እየተሻሻለ መምጣቱን ገለጹ
ጭሮ፤ ሐምሌ 10/2018(ኢዜአ)፦በምዕራብ ሐረርጌ ዞን በለውዝ ልማት የተሰማሩ አርሶ አደሮች ከዘርፉ በሚያገኙት ገቢ የኑሮ ደረጃቸው እየተሻሻለ መምጣቱን ገልጸዋል።
በዞኑ ከዚህ በፊት ከተለመዱት የሰብል ዓይነቶች ባሻገር አርሶ አደሮች በገበያ ተፈላጊ የሆኑ ምርቶችን በስፋት እያመረቱ ሲሆን በተለይም የለውዝ ልማት እየተስፋፋ መምጣቱ ተገልጿል።
በዞኑ በተለያዩ ወረዳዎች የሚገኙ አርሶ አደሮችን በለውዝ ልማት ላይ በንቃት በማሳተፍ ገቢያቸውን ይበልጥ እንዲያሳድጉ በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም የዞኑ ግብርና እና ተፈጥሮ ሀብት ጽሕፈት ቤት አስታውቋል።
ጽሕፈት ቤቱ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የአመራረት ዘዴዎችን የማሻሻልና የገበያ ትስስር የመፍጠር ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም ጠቁሟል።
በምዕራብ ሐረርጌ ዞን የሸነን ዱጎ ወረዳ ልማቱን በኩታ ገጠም እያከናወኑ ያሉ አርሶ አደሮች ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት፤ ከዚህ ቀደም በቆሎና ማሽላ ብቻ ያመርቱበት የነበረውን ማሳ በአሁኑ ወቅት ወደ ለውዝ ልማት በመቀየር ከፍተኛ ገቢ እያገኙ መሆኑን ገልጸዋል።
በወረዳው አባድር ቀበሌ የሚኖሩት አርሶ አደር ዲኔ መሐመድ ኡመር እንዳሉት፤ ባለፈው የመኸር ወቅት በለውዝ ካለሙት ሁለት ጥማድ ማሳቸው 10 ኩንታል ምርት አግኝተዋል።
ይህንኑ ምርት ለገበያ በማቅረብም ከ100 ሺህ ብር በላይ ገቢ ማግኘት መቻላቸውን ገልጸዋል።
ባገኙት ገቢ የቤት ውስጥ ፍጆታን ከማሟላት ባለፈ፣ ልጆቻቸውን እስከ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ድረስ ከፍለው ለማስተማር እንደረዳቸው ገልጸዋል።
ከዚህ ቀደም ማሽላ ብቻ ያመርቱበት የነበረውን አንድ ሄክታር የሚጠጋ ማሳቸውን ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ በለውዝ ማልማት መጀመራቸውን የገለጹት ደግሞ ሌላኛዋ የቀበሌው አርሶ አደር ወይዘሮ ሲቲ ከድር ናቸው።
ባለፈው መኸር ካለሙት ማሳ 13 ኩንታል ምርት መሰብሰባቸውንና ከዚህም ከ180 ሺህ ብር በላይ ገቢ ማግኘታቸውን ጠቁመው፤ ባገኙት ገቢም የእርሻ ግብዓቶችን ለማሟላትና እንስሳትን ገዝተው ለማድለብ መቻላቸውን አመልክተዋል።
በተመሳሳይ ወጣት ዚያድ አብዱልቃድር እንደተናገረው በአንድ ሄክታር ማሳ ላይ በኩታ ገጠም ካለማው ለውዝ ከ25 ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት ማቀዱን ገልጿል።
የሸነን ዱጎ ወረዳ እርሻና መሬት ጽሕፈት ቤት የሰብል ልማት ቡድን መሪ አቶ አብዮት ውብሸት በበኩላቸው፤ በዘንድሮው የምርት ዘመን በወረዳው ወደ ሦስት ሺህ ሄክታር የሚጠጋ መሬት በኩታ ገጠም በለውዝ እየለማ መሆኑን አስታውቀዋል።
አርሶ አደሮች በመደጋገፍና በመተጋገዝ በልማቱ ተሰማርተው ተጠቃሚነታቸውን እንዲያሳድጉ የዘርፉ ባለሙያዎች የቅርብ ክትትልና ድጋፍ እያደረጉላቸው መሆኑንም ገልጸዋል።
በተጨማሪም አርሶ አደሮች ምርታቸውን በተገቢው ወቅት ለገበያ በማቅረብ ተመጣጣኝ ዋጋ ማግኘት እንዲችሉ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን ጠቁመዋል።
በምዕራብ ሐረርጌ ዞን የሰብል ልማት አስተባባሪ አቶ ሚደቅሳ ደሬሳ በበኩላቸው፤ ዞኑ ለለውዝ ልማት ተስማሚ የአየር ንብረትና የአፈር ጸባይ ያለው በመሆኑ፣ ልማቱ ለአርሶ አደሩ ዋነኛ የገቢ ምንጭ እየሆነ መምጣቱን ተናግረዋል።
በተያዘው የመኸር ወቅትም ከ41 ሺህ በላይ አርሶ አደሮችን በማሳተፍ፣ ከ29 ሺህ 700 ሄክታር በላይ መሬት ላይ ለውዝ በኩታ ገጠም እየለማ መሆኑን ገልጸዋል።
ይህ የለውዝ ልማት በዋነኛነት በዞኑ የሸነን ዱጎ፣ ለቡ፣ ቦኬ እና ኦዳ ቡልቱም ወረዳዎች በስፋት እየተካሄደ መሆኑን የጠቀሱት አስተባባሪው፤ ከዚህም ከ700 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት ይጠበቃል ብለዋል።