ቀጥታ፡

የሀረሪ ክልል ምክር ቤት ለ2019 በጀት ዓመት 12 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር በጀት አፀደቀ

ሀረር ፤ ሐምሌ 10/2018(ኢዜአ)፦ የሀረሪ ክልል ምክር ቤት ለ2019 በጀት አመት  12 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር በጀት አፀደቀ፡፡

የክልሉ ምክር ቤት 6ኛ ዙር 5ኛ አመት 10ኛ መደበኛ ጉባኤውን እያካሄደ ነው፡፡

ምክር ቤቱ ለሁለት ቀናት እያካሄደ በሚገኘው ጉባኤ ከክልሉ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ትብብር ቢሮ የቀረበለትን የክልሉን የ2019 በጀት ዓመት 12 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር በጀት አጽድቋል።

የበጀት ረቂቁን ለምክር ቤቱ ያቀረቡት የክልሉ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ትብብር ቢሮ ሃላፊ አቶ መሀመድ ያህያ ናቸው።

ከበጀት ድልድሉ ውስጥ ከፍተኛ ድርሻ የሚይዘው የካፒታል በጀት ሲሆን፤ ይህም 65  በመቶ ድርሻ ያለው እንደሆነ ተገልጿል። እንዲሁም 35 በመቶው ለመደበኛ ወጪ ተመድቧል ።

በጀቱ የክልሉን የልማት ፍላጎት ለማሳደግ ታሳቢ ተደርጎ የተመደበ  መሆኑን ጠቁመው በተለይም በ2018 የበጀት አመት ተጀምረው ያልተጠናቀቁ ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ እንዲሁም በገጠርና በከተማ የሕዝብን የመሰረተ ልማት ጥያቄ ሊመልሱ በሚችሉ ተግባራት ላይ ትኩረት እንደሚሰጥ ተናግረዋል።

በተጨማሪም ለገጠር እና ለከተማ ኮሪደር ልማት፣ ለንፁህ መጠጥ ውሃ፣ ለትምህርትና ጤና ሁሉን አቀፍ የልማት ሥራዎች በተሳለጠ መንገድ ለማካሄድ የሚያስችል በጀት መሆኑንም አመልክተዋል። 

ምክር ቤቱም በቀረበው የ2019 ረቂቅ በጀት አዋጅ ላይ ከተወያየ በኋላ አጽድቋል።

በቀጣይም ምክር ቤቱ የተለያዩ ረቂቅ አዋጆች፣እቅዶችና ሹመቶችን ያጸድቃል ተብሎም ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም