በከተማ አስተዳደሩ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ተግባራዊ የተደረጉ የልማት ስራዎች ስኬታማ ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
በከተማ አስተዳደሩ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ተግባራዊ የተደረጉ የልማት ስራዎች ስኬታማ ናቸው
ደሴ፤ ሐምሌ 10/2018(ኢዜአ)፦በከተማ አስተዳደሩ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ተግባራዊ የተደረጉ የልማት ስራዎች ስኬታማ መሆናቸውን የደሴ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ሳሙኤል ሞላልኝ ገለፁ።
ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ሳሙኤል ሞላልኝ እንደገለጹት፣ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ሰላምን ከማጽናት ባሻገር ሰፋፊ የልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎችን ተግባራዊ ለማድረግ ተችሏል።
በዚሁ ወቅት ከተከናወኑት የልማት ስራዎች መካከል የኮሪደር ልማትን ጨምሮ የአምስት ኪሎ ሜትር አስፋልት መንገድ ግንባታ ተጠቃሽ መሆኑን አመልክተዋል።
በተጨማሪም የትምህርትና የጤና ተቋማትን ደረጃ የማሻሻል እና ሌሎች የማሕበረሰቡን ኢኮኖሚ ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ የልማት ስራዎች ተግባራዊ መደረጋቸውን ተናግረዋል።
ከዚሁ ጎን ለጎንም የአገልግሎት አሰጣጥን በቴክኖሎጂ በማስደገፍ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን መፍታት ተችሏል ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው፣ የልማት ስራው በአዲሱ በጀት ዓመትም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በ2019 በጀት ዓመት በተለይ ለመኖሪያ ቤት ግንባታ፣ ለኮሪደር ልማት፣ ገበያን ማረጋጋት፣ ለሥራ እድል ፈጠራና ሌሎችም ሰው ተኮር ፕሮጀክቶች ልዩ ትኩረት እንደሚሰጥ ነው የተናገሩት።
የደሴ ከተማ ነዋሪ የሆኑት ሸህ መሀመድ ሰይድ፣ በከተማ አስተዳደሩ በተከናወኑ የልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎች ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በተለይ በአስፋልት መንገድ ግንባታ፣ በኮሪደር ልማት፣ በገበያ ማረጋጋትና በሌሎችም የተመዘገቡ አበረታች ውጤቶች የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ያሳደጉ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
የከተማዋ ነዋሪ ወይዘሮ አያል ሰይድ በሰጡት አስተያየት፣ የከተማ አስተዳደሩ ነዋሪውን በማስተባበር ሰላም በማጽናት፣ በልማት ተጠቃሚ እንዳደረጋቸው ተናግረዋል።