ቀጥታ፡

በገጠር ሞዴል መንደሮች ምቹና ዘመናዊ አኗኗር እውን ማድረግ እንደሚቻል በተግባር እያረጋገጥን ነው - ነዋሪዎች

አርባ ምንጭ፤ ሐምሌ 10/2018(ኢዜአ)፦በገጠር ሞዴል መንደሮች ምቹና ዘመናዊ አኗኗር እውን ማድረግ እንደሚቻል በተግባር እያረጋገጥን ነው ሲሉ በጋሞ ዞን ሐመሳ ቀበሌ የኢሊሎ ሞዴል የገጠር መንደር ነዋሪዎች ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጋሞ ዞን የገጠር ኮሪደር ልማት አካል የሆነውን የሀማሳ ሞዴል መንደር መመርቃቸው  ይታወሳል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወቅቱ እንዳሉት መንደሩ የአርሶ አደሩን ኑሮና ምርታማነት ለማሻሻል የሚያግዙ ዘመናዊ የመታጠቢያ ክፍሎች፣ የእንስሳት ማደሪያ፣ የአትክልት ስፍራ፣ የባዮ ጋዝ እና የንብ ቀፎዎችን ያሟሉ በመሆኑ የነዋሪዎችን ተጠቃሚነት ያረጋግጣል። 

ይህ ሞዴል መንደር የገጠሩን ማህበረሰብ ክብር፣ ምቾት እና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋገረ መሆኑንም ማንሳታቸው የሚታወስ ነው።

ኢዜአ ካነጋገራቸው የመንደሩ ነዋሪዎች መካከል አቶ አስፋው አያኖ እንዳሉት ከዚህ ቀደም በግንዛቤ እጥረት ገንዘባቸውን በአግባቡ መጠቀም ባለመቻላቸው ኑሯቸው ያልዘመነ እንደበር አስታውሰዋል።


 

አሁን በአካባቢያቸው የተገነባው ሞዴል የገጠር መንደር መኖሪያ ቤታቸውን ከማዘመን ባለፈ አኗኗራቸውን ለመቀየር ማስቻሉን ተናግረዋል።

በግቢያቸው ውስጥ የተለያዩ የጓሮ አትክልትና ፍራፍሬዎችን ከማልማት ባለፈ በዶሮ እና ፍየል እርባታም ተጠቃሚነታቸውን እያሳደጉ መምጣታቸውን ገልጸዋል።

ባለቤታቸው ወይዘሮ ወይንሸት ሀድጉም በገጠር ሞዴል መንደሩ የፀሐይ እና የኤሌክትሪክ ኃይል አማራጭ እንደሚጠቀሙ ተናግረዋል።


 

ለብቻው የተዘጋጀ የእንስሳት ማደሪያ ያለውና ለዘመናዊ ኑሮ የሚያስፈልጉ ቁሶች የተሟሉለት በመሆኑ ኑሯቸው እየተሻሻለ መምጣቱን ገልጸዋል።

አቶ ደስታ ኡሊሶ እና ባለቤታቸው ወይዘሮ ደግነሽ ደምሴ፤ በበኩላቸው ከዚህ ቀደም ለኑሮ አስፈላጊ ግብአቶች በሌለው መኖሪያ ቤት ውስጥ በችግር ይኖሩ እንደነበር አንስተዋል።


 

በሐመሳ ቀበሌ ኢሊሎ መንደር የገነቡት ሞዴል መኖሪያ ቤት ኤሌክትሪክ ሃይልን ጨምሮ ሌሎች ግብአቶች የተሟላላት በመሆኑ ምቹና ዘመናዊ ኑሮ ለመምራት እንዳስቻላቸው ተናግረዋል። 

ሞዴል የገጠር መንደሩ ዘመናዊነትን ለተላበሰ የኑሮ ዜይቤ መነሻ ሆኖናል ያሉት ደግሞ አቶ ከበደ ገቢሳ ናቸው።


 

አርሶ አደሩ ሀብት እያለው በግንዛቤ እጥረት ምክንያት ኑሮው ሳይዘምን መቆየቱን አስታውሰው፣ ሞዴል መንደሩ ንጹህና ሁሉም መሠረተ ልማቶች የተሟሉለት መሆኑን ተናግረዋል።

የመንደሩ ነዋሪዎች ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በገጠር ኮሪደር እሳቤ የአርሶ አደሮችን ሕይወት ለማሻሻልና አኗኗራቸው እንዲዘምን በቁርጠኝነት ላደረጉት አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም