ቀጥታ፡

የብልፅግና ፓርቲ እሳቤዎችን በተግባር በመተርጎም ውጤታማ ተግባራት ተከናውነዋል 

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 10/2018(ኢዜአ)፦ አመራሩ የብልፅግና ፓርቲ እሳቤዎችን በተግባር በመተርጎም ውጤታማ የመንግሥትና የፓርቲ ተግባራት ማከናወኑን በብልፅግና ፓርቲ የሐረሪ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ጌቱ ወዬሳ ገለጹ።

አቶ ጌቱ ወዬሳ በተጠናቀቀው በጀት አመት በተከናወኑ ተግባራት ዙሪያ በሰጡት መግለጫ በ2018 በጀት ዓመት ፓርቲውን በአሰራር፣ በሰው ሀይል እና በአደረጃጀት የማጠናከር ስራ ተሰርቷል ብለዋል።

አባልና አመራሩ በፓርቲው እሳቤዎችና አቋሞች ላይ የጠራ ግንዛቤና አመለካከት እንዲኖረው በማድረግ በኩል አበረታች ስራዎች መሰራታቸውንም አክለዋል።

ገዥ ትርክትን ለማስረጽ በተሰራ ስራ ውጤት መገኘቱን ጠቁመው የአመራሩና የአባላት የአስተሳሰብና የተግባር አንድነት በጉልህ የታየበት በመሆኑም ተደራራቢ ተልዕኮዎች ስኬታማ መሆናቸውን አብራርተዋል።

አባላት የተግባር ተልዕኮዎችን ውጤታማ በማድረጋቸው ለክልሉ ፈጣን ዕድገት ጉልህ አሻራ ማሳረፍ መቻሉን ገልፀዋል።

የፓርቲውን እሳቤዎች በተግባር በመተርጎም በየዘርፉ የተመዘገቡ ድሎች በቁርጠኛ አመራር የተመሩ፣ የሁሉም አሻራ ያረፈባቸው መሆናቸውን ተናግረዋል።

በበጀት ዓመቱ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫን ጨምሮ በርካታ ግቦች ማሳካት መቻሉን ጠቁመው የሴቶችንና የወጣቶችን ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ለማሳደግ በተሰራ ስራም ውጤት ተገኝቷል ነው ያሉት።

በቀጣይም በአገልግሎት አሰጣጥ የህዝብን እርካታ ማሳደግ እንዲሁም ብልሹ አሰራሮችን ከማስወገድ አንፃር በልዩ ትኩረት ይሰራል ብለዋል።

አመራሩም የተገኙ ስኬቶች ተጠናክረው እንዲቀጥሉና የብልጽግና ግቦች እንዲሳኩ በላቀ ቁርጠኝነት መንቀሳቀስ እንዳለበት ነው ያስገነዘቡት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም