ቀጥታ፡

ሞሪሺየስ እና ኢትዮጵያ ትብብራቸውን ማጠናከር የሚችሉባቸው ሰፊ እድሎች አሉ - የሞሪሺየስ ፕሬዝዳንት ድሃራምቢር ጎኩል

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 10/2018(ኢዜአ)፦ ሞሪሺየስ እና ኢትዮጵያ ጤና እና ትምህርትን ጨምሮ የሁለትዮሽ ትስስራቸውን ማጎልበት የሚችሉባቸው አዳዲስ ዘርፎች መኖራቸውን የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ድሃራምቢር ጎኩል ገለጹ።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከሐምሌ 5 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ አበባና በፖርት ሉዊስ መካከል በሳምንት ሦስት ጊዜ የሚደረግ ቀጥታ የመንገደኞች በረራ በይፋ አስጀምሯል።

የሞሪሺየስ ፕሬዝዳንት ዳህራምቢር ጎኩል የአየር መንገዱን የቀጥታ በረራ መጀመር አስመልክቶ ለፐልስ ኦፍ አፍሪካ ሚዲያ (Pulse of Africa Media POA) እንደገለጹት፤ ጠንካራ የአየር ትስስር የአፍሪካን የኢኮኖሚ አቅም ለማጎልበት ወሳኝ ነው።

አየር መንገዱ ወደ ሞሪሺየስ የጀመረው የቀጥታ በረራ በሀገራቱ መካከል በቱሪዝም፣ በንግድ፣ በኢንቨስትመንትና በሰው ኃይል ልማት ዘርፎች አዳዲስ ዕድሎችን እንደሚፈጥር አመልክተዋል።

ጠንካራ የአየር ትስስር የአፍሪካን ሙሉ የኢኮኖሚ አቅም ለመጠቀም ወሳኝ መሆኑን ገልጸው በረራው መጀመሩ የአፍሪካ ህብረት ይበልጥ የተቀናጀች አህጉር ለመፍጠር የሰነቀውን ራዕይ የሚያሳልጥ ነው ብለዋል።

ጠንካራ የአየር ትስስር የአፍሪካን ሙሉ የኢኮኖሚ አቅም ለመጠቀም ወሳኝ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል።

በአፍሪካ አህጉር ከሚገኙ ታላላቅ ተግዳሮቶች መካከል የትስስር አለመጠናከር ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ ሞሪሺየስን ከኢትዮጵያ ጋር በማገናኘት፣ አፍሪካ ይህንን የቆየ እንቅፋት ለመቅረፍ ተጨባጭ እርምጃዎችን እየወሰደች መሆኑን የሚያሳይ ነው ብለዋል።

ይህ አዲስ የበረራ መስመር ከመንገደኞች ማጓጓዝ ባለፈ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የረጅም ጊዜ አጋርነት ለማጠናከር ትልቅ አቅም እንደሆነም አብራርተዋል።

ሞሪሺየስ ለዓለም አቀፍ ባለሀብቶችና የንግድ ተቋማት ዋነኛ የአፍሪካ መግቢያ በር ለመሆን እየሰራች መሆኑን ጠቁመውም፤ ይህንን ራዕይ ለማሳካት ጠንካራ የአየር ትስስር መፍጠር ቁልፍ ተግባር ነው ሲሉ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ያለው ሰፊ የአፍሪካና የዓለም አቀፍ የበረራ ተደራሽነት በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የንግድና የኢንቨስትመንት ፍሰት በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚያሳድገውም ጠቁመዋል።

የጭነት ትራንስፖርት (ካርጎ) ከአፍሪካ ዋና ዋና የአቅርቦት ማነቆዎች አንዱ መሆኑን ጠቁመው፣ አዲሱ አጋርነት በአህጉሪቱ ያለውን የዕቃዎች ዝውውር ለማሻሻል ትልቅ ተስፋ እንደሚሰጥ ተናግረዋል።

በጋራ መሥራታችን ይህንን የአቅርቦትና የዕቃዎች ዝውውር ችግር ለመፍታት ሰፊ ዕድል ይፈጥርልናል ሲሉም አክለዋል።

የኢትዮጵያ የአቪዬሽን ማሰልጠኛ ለሞሪሺየስ ወጣቶች የአውሮፕላን አብራሪነትን ጨምሮ በሌሎች የአቪዬሽን የሙያ ዘርፎች የላቀ የአቅም ግንባታና የስልጠና ዕድሎችን እንደሚከፍት ጠቁመዋል።

በቀጣይም በትምህርት፣ በጤና እና በሰማያዊ ኢኮኖሚ (Blue Economy) ዘርፎች ዕውቀትን፣ ቴክኖሎጂንና ልምድን በመለዋወጥ በጋራ ለመሥራት ሰፊ ዕድል እንዳለ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሐምሌ 5 ቀን 2018 ዓ.ም ወደ ሞሪሺየስ በሳምንት ሶስት ቀናት ቀጥታ የመንገደኞች በረራ መጀመሩ ይታወቃል።

ይህም መንገደኞች ወደ አፍሪካ፣ አውሮፓ፣ እስያ፣ መካከለኛው ምስራቅ እና አሜሪካ በቀላሉ እንዲጓዙ በማድረግ የአህጉሪቱን ትስስር እንደሚያጠናክር ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም