ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ በመቅረጽ፣ ለአረንጓዴ ልማት ያላትን ቁርጠኝነት በተግባር አሳይታለች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ በመቅረጽ፣ ለአረንጓዴ ልማት ያላትን ቁርጠኝነት በተግባር አሳይታለች
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 9/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ በመቅረጽ፣ ለአረንጓዴ ልማት ያላትን ፅኑ ቁርጠኝነት በተግባር ማሳየቷን የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ፍቃዱ ፀጋ ገለጹ።
በኢትዮጵያ የአረንጓዴ አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንተርፕራይዞችን ለማጠናከር ለተቀረጸው የምርምር ፕሮጀክት የተዘጋጀ የማስጀመሪያ አውደ ጥናት ተካሂዷል።
በአውደ ጥናቱ መክፈቻ የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ፍቃዱ ፀጋ እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ በመቅረጽ፣ ለአረንጓዴ ልማት ያላትን ፅኑ ቁርጠኝነት በተግባር አሳይታለች።
ይህም በታዳሽ ኃይል መስፋፋት፣ በዘላቂ ግብርና እና ለአካባቢ ጥበቃ ተስማሚ በሆኑ የኢንዱስትሪ እንቅስቃሴዎች ውስጥ በግልጽ ይንጸባረቃል ብለዋል።
አረንጓዴ ኢኮኖሚን መገንባት የመንግሥትን ጥረት ብቻ ሳይሆን የሁሉንም አካላት ንቁ ተሳትፎ ይጠይቃል ነው ያሉት።
በተለይም አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንተርፕራይዞችን ማሳተፍ ወሳኝና አማራጭ የሌለው ተግባር መሆኑን ገልጸዋል።
እነዚህ ኢንተርፕራይዞች ለኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ሽግግር፣ ለሥራ ዕድል ፈጠራ፣ ለእሴት ሰንሰለት ዕድገት፣ ለሀገር ውስጥ ምርት እንዲሁም ለኢኮኖሚ ብዝኃነት ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳላቸውም አስገንዝበዋል።
ወደ አረንጓዴ ማኑፋክቸሪንግ የሚደረገው ሽግግር የመንግስት፣ የግልና ሌሎች ባለድርሻ አካላትን የተቀናጀ አካሄድ ይፈልጋል ብለዋል።
በኢንስቲትዩቱ በአምራች ዘርፍ የማዕድን ዘርፍ ክፍል ኃላፊ እና መሪ ተመራማሪ ነጻነት ጆቴ (ዶ/ር) በዓለም አቀፍ ደረጃ አካባቢን የማይበክልና ዘላቂ የምርት ሥርዓት መገንባት አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል።
በኢትዮጵያ የሚገኙ የአረንጓዴ ማኑፋክቸሪንግ ኢንተርፕራይዞችን የሚዳስስ ጥናት እንደሚደረግ ጠቁመው የጥናቱ ዋና ዓላማ የኢንተርፕራይዞቹን ወቅታዊ ሁኔታ፣ ዕድሎችንና ፈተናዎችን በማመላከት ተወዳዳሪነታቸውን ማሳደግ ነው ብለዋል።
በአፍሪካ ክላይሜት ፋውንዴሽን የፕሮጀክት ማናጀር ሳህሌ ታምሩ ፋውንዴሽኑ በታዳሽ ኃይል፣ አረንጓዴ ኢንዱስትሪ፣ የትራንስፖርትና የፋይናንስ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ጥናቶችና ምርምሮችን እየደገፈ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ዘርፍ ያላትን እምቅ አቅም በመጠቀም በዓለም አቀፍ ገበያ በአረንጓዴ ኢኮኖሚ ተወዳዳሪነቷንና ተጠቃሚነቷን ለማሳደግ ጥናቱ አስተዋጽኦ የሚያደርግ በመሆኑ በጋራ እንሰራለን ብለዋል።