ከኢትዮጵያ ጋር የሁለትዮሽ ግንኙነትን ለማጠናከር የተከናወኑ ተግባራት ውጤታማ ናቸው - በኢትዮጵያ የኦስትሪያ እና ቼክ ሪፐብሊክ አምባሳደሮች - ኢዜአ አማርኛ
ከኢትዮጵያ ጋር የሁለትዮሽ ግንኙነትን ለማጠናከር የተከናወኑ ተግባራት ውጤታማ ናቸው - በኢትዮጵያ የኦስትሪያ እና ቼክ ሪፐብሊክ አምባሳደሮች
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 9/2018(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ የኦስትሪያ እና የቼክ ሪፐብሊክ አምባሳደሮች በሀገሪቱ በነበራቸው የሥራ ቆይታ የሁለትዮሽ ግንኙነትን ለማጠናከር የተከናወኑ ተግባራት ውጤታማ መሆናቸውን ገለጹ።
አምባሳደሮቹ በኢትዮጵያ በነበራቸው የሥራ ቆይታ፣ በሀገራቱ መካከል ያለውን የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማጠናከር የተከናወኑ ተግባራት ውጤታማ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ የነበራቸውን የስራ ጊዜ ያጠናቀቁት የኦስትሪያ አምባሳደር ሲሞን ክናፕን (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ በኢትዮጵያ በቆዩባቸው አራት ዓመታት የሀገሪቱን ውብና የተለያዩ ባህላዊና ተፈጥሯዊ መስህቦች መጎብኘት በመቻላቸው እጅግ አስደሳች ጊዜ አሳልፈዋል።
ኢትዮጵያ እና ኦስትሪያ ለረጅም ዓመታት ታሪካዊና ጠንካራ ወዳጅነት እንዳላቸው ጠቅሰው፤ በኢኮኖሚና በንግድ ዘርፍ ያለውን ግንኙነት ይበልጥ ለማሳደግ ሰፋፊ ዕድሎች መኖራቸውን ጠቁመዋል።
በቆይታቸውም በርካታ የኦስትሪያ ኩባንያዎች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው የሀገሪቱን የኢንቨስትመንት አማራጮች እንዲገነዘቡ የጋራ አጋርነትና የንግድ ትስስር እንዲመሰርቱ ምቹ ሁኔታ መፈጠሩንም ገልጸዋል።
ይህ ግንኙነት ወደፊት ይበልጥ እንደሚጠናከር ተስፋ እንዳላቸውም ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ የነበራቸውን የስራ ጊዜ ያጠናቀቁት የቼክ ሪፐብሊክ አምባሳደር ሚሮስላቭ ኮሴክ በበኩላቸው፤ ላለፉት አራት ዓመታት በኢትዮጵያ ያደረጉት ቆይታ እጅግ ፍሬያማና ስኬታማ እንደነበር ገልጸዋል።
በተለይም በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የንግድ፣ የኢኮኖሚና የባህል ትብብር ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን አስረድተዋል።