ቀጥታ፡

ሕገ-ወጡ የሕወሓት ቡድን በትግራይ ክልል እየፈጸመ ያለው አስገዳጅ ወታደራዊ አፈሳና ምልመላ በሕዝቡ ላይ ሰብዓዊ ጉዳትና ጉስቁልና እያደረሰ ነው

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 9/2018(ኢዜአ)፦ ሕገ-ወጡ የሕወሓት ቡድን በትግራይ ክልል እየፈጸመ ያለው አስገዳጅ ወታደራዊ አፈሳና ምልመላ በሕዝቡ ላይ ሰብዓዊ ጉዳትና ጉስቁልና እያደረሰ መሆኑን የትግራይ የሰላምና ለውጥ ምክር ቤት አስታወቀ።

ሕገ-ወጡ የሕወሓት ቡድን በትግራይ ክልል ህዘብ ላይ የሚፈፅመውን አፈናና ጭቆና የሚያወግዝ ሰላማዊ ሰልፍ ቅዳሜ ሐምሌ 11 ቀን 2018 ዓ.ም ከማለዳው 12፡00 ሰዓት ጀምሮ እንደሚያካሂድ ምክር ቤቱ ገልጿል።

የምክር ቤቱ የሚዲያና የህዝብ ግንኙነት አስተባባሪ ከበደ አሰፋ በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት፤ ''አፈሳ ይቁም፥ ሰላም ይስፈን” በሚል መሪ ሃሳብ ሰላማዊ ሰልፉ በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ ይካሄዳል።

ይህንን ሰልፍ የጠራው የትግራይ የሰላምና የለውጥ ምክር ቤት ሲሆን፣ የሰልፉ አስተባባሪዎች ለዝግጅቱ ከሚመለከተው የመንግሥት አካል ሕጋዊ ዕውቅና እና ፈቃድ ማግኘታቸውን ገልጸዋል።

ሰላማዊ ሰልፉም በክልሉ በሕገ-ወጡ የሕወሓት ቡድን የሚፈጸመውን እኩይ ተግባር ለማጋለጥ ያለመ መሆኑን ተናግረዋል።

ሕገ-ወጥ ቡድኑ በትግራይ ክልል ወጣቶች ላይ በሚፈፅመው አስገዳጅ ወታደራዊ ምልምላ እና እየደረሰ ያለውን ሰብዓዊ ጉስቁልና እንዲሁም እያደረሰ ያለውን ሥነ-ልቦናዊ ጫና በፅኑ የሚቃወም መሆኑን አንስተዋል።

በክልሉ ያለአግባብ ታስረው ለሚገኙ ንጹሀን ዜጎች በተለይም ለእናቶች ድምፅ በመሆን የሚደርስባቸውን ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ማስገንዘብም የሰልፉ ዓላማ መሆኑን ጠቁመዋል።

ሕገ-ወጡ የሕወሓት ቡድን ወጣቶችን በግዳጅ ለውትድርና በመመልመል ሕዝብን ለዳግም እልቂት ለመዳረግ እየተዘጋጀ መሆኑንም ገልጸዋል።

በክልሉ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን፣ የፌዴራል መንግሥት በክልሉ ሕግ እንዲያስከብር እንዲሁም ቡድኑ የፕሪቶሪያን የሰላም ስምምነት በተሟላ ሁኔታ ተግባራዊ እንዲያደርግ መልዕክት እንደሚተላለፍም ተናግረዋል።

በዕለቱ በሚካሄደው ሰልፍ ላይ በአዲስ አበባና በአካባቢው የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች፣ ሁሉም ሰላም ወዳድ የኢትዮጵያ ዜጎች በነቂስ እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል።

የትግራይ ክልል ሕዝብም በዕለቱ ከቤቱ ባለመውጣት የተቃውሞው ተካፋይ እንዲሆንና ድጋፉን በተግባር እንዲገልጽ አስተባባሪዎቹ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም