ቀጥታ፡

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በበጀት ዓመቱ ከ35 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ ወደ ተግባር ተገብቷል

ቡታጅራ ፤ሐምሌ 9 /2018 (ኢዜአ)፦ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በተያዘው በጀት ዓመት ከ35 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ ወደ ተግባር መገባቱን የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ገለጸ።

የክልሉ ገቢዎች ቢሮ የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማና የ2019 በጀት ዓመት የገቢ ዕቅድ ተግባቦት ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ በቡታጅራ ከተማ ተካሂዷል።


 

የቢሮው ኃላፊ ወይዘሮ ቀመሪያ ረሻድ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ በክልሉ የተጀመሩ የልማት ሥራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ገቢን አሟጦ የመሰብሰብ ሥራው ተጠናክሮ ቀጥሏል።

በ2019 በጀት ዓመት የክልሉን ገቢ የማመንጨት አቅምንና የማኅበረሰቡን የልማት ጥያቄ ታሳቢ በማድረግ ከ35 ቢሊዮን ብር በላይ ለመሰብሰብ የሚያስችል የገቢ ዕቅድ ተዘጋጅቶ ወደ ተግባር ስለመገባቱም ተናግረዋል።

የድጋፍና ክትትል ሥራን በማጠናከር፣ አገልግሎት አሰጣጥን በቴክኖሎጂ በመደገፍ ቀልጣፋ አገልግሎትን ተደራሽ በማድረግ ዕቅዱን ለማሳካት ይሠራል ነው ያሉት፡፡

ከተሳታፊዎች መካከል የስልጤ ዞን የገቢዎች መምሪያ ኃላፊ አቶ ከድር አደም በሰጡት አስተያየት፤ ግብር ለአካባቢው ማኅበረሰብ የልማት ጥያቄ ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ያለው ሚና ከፍተኛ ነው።


 

በዞኑ በ2018 በጀት ዓመት የተገኘውን ልምድ በመቀመር በ2019 በጀት ዓመት ከ6 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ መታቀዱንም አመልክተዋል።

በልዩ ወረዳው ያለውን የገቢ አማራጭ አሟጦ በመሰብሰብ ወጪን በራስ ገቢ ለመሸፈን ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ እንደሚገኝ የተናገሩት ደግሞ የጠምባሮ ልዩ ወረዳ ገቢዎች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ እንዳሻው አበራ ናቸው።

በልዩ ወረዳው እየተመዘገበ ያለውን ዕድገት ለማስቀጠልም በ2019 በጀት ዓመት ከ505 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ መታቀዱን ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም