የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ የጋራ አሸናፊነትን የሚያጎናጽፍ የብሩህ ዘመን ማብሰሪያ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ የጋራ አሸናፊነትን የሚያጎናጽፍ የብሩህ ዘመን ማብሰሪያ ነው
አዲስ አበባ፤ሐምሌ 9 /2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ጠንካራ ሀገረ መንግሥት በመገንባት የጋራ አሸናፊነትን የሚያጎናጽፍ የብሩህ ዘመን ማብሰሪያ ወሳኝ አጀንዳ መሆኑን የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶችና የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ዋናው ጉባኤ ከትናንት ረቡዕ ሐምሌ 08 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ መካሄድ ጀመረ ሲሆን፤ ከወረዳ እስከ ክልል፣ ከፌዴራል እስከ ውጭ ሀገራት የተውጣጡ የህዝብ ወኪሎችም በአዲስ አበባ አዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል እየመከሩ ነው።
በጉባኤው አራት ሺህ የህዝብ ተወካዮች እየተሳተፉ ሲሆን፤ በሀገር ግንባታ፣ በመንግሥት አደረጃጀትና ቅርጽ፣ በፖለቲካ ሥርዓት፣ በምርጫ ሥርዓትና ውክልና፣ በፌዴራል ከተሞች (አዲስ አበባና ድሬዳዋ) አስተዳደር፣ በሃይማኖት ጉዳዮች፣ በተቋማት ግንባታ፣ በሕግ የበላይነትና ሰብዓዊ መብቶች፣ በማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች፣ በአርሶ አደርና አርብቶ አደር ጥያቄዎች እንዲሁም በሙስና፣ በመልካም አስተዳደርና በሰላም ግንባታ ዐበይት አጀንዳዎች ላይ እየመከሩ ይገኛሉ።
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችና የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የጉባኤው ዐበይት አጀንዳዎች የኢትዮጵያን የዘመናት አለመግባባቶች በመፍታት ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት የሚያስችሉ ናቸው።
በዚህም የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ጠንካራ ሀገረ መንግሥት በመገንባት በዜጎች መካከል የጋራ አሸናፊነትን የሚያጎናጽፍ የብሩህ ዘመን ማብሰሪያ አጀንዳ መሆኑን አንስተዋል።
የኢትዮጵያ ሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት አሕመድ ሁሴን፤ ሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች ዜጎች በኢትዮጵያ ጉዳይ ስልጡን ምክክር ለማድረግ ከወሰኑበት ጊዜ ጀምሮ ንቁ ተሳትፎና ድጋፍ ሲያደርጉ መቆየታቸውን ገልጸዋል።
የሀገራዊ ምክክሩ ዐበይት አጀንዳዎች የኢትዮጵያንና ህዝቦቿን ነባራዊ ሁኔታ ታሳቢ በማድረግ የተቀረጹ በመሆናቸው ውስብስብ ችግሮችን በምክክር ለመፍታት ትልቅ አቅም አላቸው ብለዋል።
የዩቡንቱ ወጣቶች ለሰላም ጥምረት ሰብሳቢና የጣምራ ማህበራዊ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ብሩክ ይርጋለም፤ የጉባኤው አጀንዳዎች የወጣቶችን የተሻለ ሀገር የመገንባት ፍላጎት ያገናዘቡ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
ወጣቶች በአጀንዳ ማሰባሰብና በተሳታፊ ልየታ ሂደት ንቁ ተሳትፎ ማድረጋቸውንና ያቀረቧቸው ሃሳቦች በስምንቱ ዐበይት አጀንዳዎች ስር በንዑስ አጀንዳነት መካተታቸውን ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶች ማህበር ፕሬዝዳንት በረከት ብርቢርሳ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር የወጣቶችን ተሳትፎ በተግባር ያረጋገጠ መሆኑን ገልጸዋል።
በጉባኤው የተካተቱት ዐበይት አጀንዳዎች ለዘመናት የቆዩ የተዛቡ ትርክቶችን በማረም፣ የወጣቶችን ዘላቂ ሰላምና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ወሳኝ መሆናቸውን አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ ሴቶች ፌዴሬሽን ዋና ዳይሬክተር ገነት ስዩም፤ ሴቶች በሀገራዊ ምክክሩ ብሔራዊ መግባባትን በመፍጠር ረገድ የራሳቸው የሆነ ድርሻ እንዳላቸው ገልጸዋል።
በዚሁ መሰረት በአጀንዳ ማሰባሰብና በተሳታፊ ልየታ ወቅት ሴቶች ንቁ ተሳትፎ ማድረጋቸውንና በዋናው ጉባኤም በወኪሎቻቸው አማካኝነት ገንቢ ሚና መጫወት መጀመራቸውን አስታውቀዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ሴቶች ማኅበር ፕሬዝዳንት እናትዓለም እንዳለ በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ ለዘመናት በዘለቁ ግጭቶች ሴቶች ቀዳሚ ሰለባ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
በመሆኑም በዋናው ጉባኤ የሕግና ፍትሕ፣ የሰብዓዊ መብትና የፖለቲካ ተሳትፎን የተመለከቱ የሴቶች አጀንዳዎች መለየታቸው ለችግሮቻቸው መፍትሔ እንደሚያመጣ እምነታቸውን ገልጸዋል።
የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በበኩላቸው፤ ዋናው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ለዘመናት የቆዩና የማያግባቡ ጉዳዮችን በጥልቀት በመምከር ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር ትልቅ ዕድል እንደሆነ ገልጸዋል።
አቶ ያሬድ ደምሌ እንደገለጹት፤ በምክክር ጉባኤው ሀገርን ከፍተኛ ዋጋ ያስከፈሉ የጦርነትና የግጭት ምንጮችን በሃሳብ የበላይነት መፍታትና ጠንካራ ሀገረ መንግሥት መገንባት ይቻላል።
ሌላኛው አስተያየት ሰጪ ኃይሌ ባህረ በበኩላቸው፤ ምክክሩ የኢትዮጵያን ሕብረ-ብሔራዊ አንድነት የሚያስቀጥልና ጠንካራ መግባባትን የሚፈጥር ቁልፍ ዕድል መሆኑን አስረድተዋል።
የኢትጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤም ጠንካራ ብሔራዊ መግባባትና ዕድገትን በማስቀጠል ዘላቂ ሰላምና ልማትን የሚያፋጥን ድልድይ መሆኑንም አብራርተዋል።