ቀጥታ፡

ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ የሥራ ጊዜያቸውን ያጠናቀቁትን በኢትዮጵያ የኦስትሪያ እና የቼክ ሪፐብሊክ አምባሳደሮች አሰናበቱ

አዲስ አበባ፤ሐምሌ 9 /2018 (ኢዜአ)፦ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ በኢትዮጵያ የሥራ ጊዜያቸውን ያጠናቀቁትን በኢትዮጵያ የኦስትሪያ አምባሳደር ሲሞን ክናፕን (ዶ/ር) እና የቼክ ሪፐብሊክ አምባሳደር ሚሮስላቭ ኮሴክን አሰናብተዋል።

አምባሳደሮቹ በኢትዮጵያ በነበራቸው የሥራ ቆይታ፣ በሀገራቱ መካከል ያለውን የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማጠናከር የተከናወኑ ተግባራት ውጤታማ እንደነበሩ ገልጸዋል።


 

የኦስትሪያ አምባሳደር ሲሞን ክናፕን (ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በቆይታቸው የኢትዮጵያና ኦስትሪያን ታሪካዊና ጠንካራ የሁለትዮሽ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር የሚያስችሉ ስራዎች ተሰርተዋል።

ዲፕሎማሲያዊ ቆይታቸው ፍሬያማ እንደነበር ያመለከቱት አምባሳደሩ፣ ለተደረገላቸው ሁለንተናዊ ድጋፍና ትብብር ለኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።


 

በተመሳሳይ፣ ተሰናባቹ በኢትዮጵያ የቼክ ሪፐብሊክ አምባሳደር ሚሮስላቭ ኮሴክ፤ የሀገራቱን የንግድና ኢንቨስትመንት ትብብር ወደ ላቀ ምዕራፍ የሚያሸጋግር ስኬታማ ቆይታ እንደነበራቸው ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ በነበራቸው ቆይታ የተከናወኑ የትብብር ስራዎች፣ በቀጣይም ይበልጥ ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ጽኑ እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም