ቀጥታ፡

የቡሌሆራ ዩኒቨርሲቲ ለምርምር ስራዎቹ ተደራሽነት ከኢዜአ ጋር ያለውን አጋርነት አጠናክሮ ይቀጥላል

አዲስ አበባ ፤ ሐምሌ 9/2018 (ኢዜአ) ፦ የቡሌሆራ ዩኒቨርሲቲ በምርምርና ሃገር በቀል እውቀቶች የሚያከናውናቸውን ስራዎች ተደራሽነት ለማስፋት ከኢዜአ ጋር ያለውን አጋርነት አጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ተመስገን ደበሎ (ዶ/ር) ገለጹ።

የቡሌሆራ ዩኒቨርሲቲና የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በምርምር ስራዎችና ሀገር በቀል እውቀቶች ተደራሽነት ላይ በጋራ ለመስራት ተስማምተዋል።


 

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት በስምምነቱ ወቅት እንደገለጹት፤ ኢዜአ ሰፊ ተደራሽነት ያለው ተጽዕኖ ፈጣሪ የመገናኛ ብዙሃን ተቋም ስለሆነ ስምምነቱ ለዩኒቨርሲቲው ትልቅ ዋጋ አለው።

ዩኒቨርሲቲው ከሶስተኛው ትውልድ ዩኒቨርሲቲዎች መካከል እንደሚመደብ ያነሱት ፕሬዝዳንቱ፤ የመማር ማስተማር፣ የምርምር እና የማህበረሰብ አገልግሎት ስራዎችን እያከናወነ ይገኛልም ብለዋል።

በተለይም በግብርና፣ በማዕድን እና ከገዳ ስርዓት ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ሀገር በቀል እውቀቶች ከዘመናዊ የትምህርት ስርዓት ጋር በማቀናጀት ለሀገር እድገት የሚጠበቅበትን እየተወጣ መሆኑንም አስረድተዋል።

ስምምነቱ ዩኒቨርሲቲው የሚያከናውናቸውን ተግባራት በሀገር አቀፍ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ በስፋት ለማስተዋወቅ፣ እንዲሁም ከባለድርሻ አካላት ጋር ያለውን ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር የሚያስችል አቅም እንደሚፈጥር ዶክተር ተመስገን ገልጸዋል።


 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሰይፈ ደርቤ በበኩላቸው ከ85 ዓመታት በላይ የካበተ ልምድ ያለው ኢዜአ፤ በለውጥ ሂደት ላይ እንደሚገኝ አስታውሰው ሁለቱ ተቋማት የፈጸሙት ስምምነትን የያዟቸውን የጋራ ግቦች ለማሳካት ወሳኝ ምዕራፍ መሆኑን ገልጸዋል።

በቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ አካባቢ የሚገኙ እምቅ የተፈጥሮ ሀብቶችና ሀገር በቀል እውቀቶችን በአህጉራዊ ደረጃ ለማስተዋወቅ ኢዜአ በዘርፉ ካለው የላቀ አቅም አኳያ ተመራጭ አጋር መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

ስምምነቱ በመደመር እሳቤ ሀገር በቀል እውቀትን ተጠቅሞ ብልፅግናን ለማረጋገጥ ለተያዘው ግብ ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው አስረድተዋል።

ኢዜአ ከዜና ስራዎች ባሻገር በዓለም አቀፍ ምርምር፣ በዶክመንተሪ እና በተለያዩ ፕሮግራሞች ላይ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው ዩኒቨርሲቲው በአፍሪካ ደረጃ ተጠቃሽ ተቋም ለመሆን ለሚያደርገው ጥረት አጋዥ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም