የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ዘመናዊ የአሰራር ሥርዓት የተገልጋዩን እርካታ እያሳደገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ዘመናዊ የአሰራር ሥርዓት የተገልጋዩን እርካታ እያሳደገ ነው
አዲስ አበባ፤ሐምሌ 9 /2018 (ኢዜአ)፦ የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ዘመናዊ የአሰራር ሥርዓት ምቹ የሥራ ከባቢን በመፍጠር የተገልጋዩን እርካታ እያሳደገ መሆኑን የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር ሰላማዊት ዳዊት ገለጹ።
የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ሰላማዊት ዳዊት፤ ተቋሙ በ2018 በጀት ዓመት ያከናወናቸውን ተግባራት አስመልክተው ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም ተቋሙ ዘመኑን የሚመጥን የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን በማስፋፋት፣ የአሰራር ሥርዓቱን በማዘመን እና ምቹ የስራ ከባቢን በመፍጠር የተገልጋዩን እርካታ የሚያሳድጉ ተጨባጭ ለውጦች ማምጣቱን ገልጸዋል።
የፓስፖርት እና የቪዛ አገልግሎትን ጨምሮ ሌሎች የይለፍ ሰነዶች በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ተደግፈው በጥራት እና በደህንነት እንዲመረት መደረጉን ጠቅሰው በዚህም በበጀት ዓመቱ ከ1 ነጥብ 6 ሚሊዮን በላይ ፓስፖርቶች ታትመው ለዜጎች መሰራጨታቸውን ጠቅሰዋል፡፡
የኤሌክትሮኒክ ፓስፖርት መስጫ ማዕከላትን ከነበሩበት 12 ወደ 23 በማሳደግ ተደራሽነቱን ማስፋፋት መቻሉን ጠቅሰው በአየር እና በየብስ የድንበር መቆጣጠሪያ ጣቢያዎች ከ7 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ መንገደኞች ቀልጣፋ አገልግሎት መሰጠቱን ጠቅሰዋል፡፡
የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ከሚሰጣቸው አገልግሎቶች 42 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡንም ጠቁመዋል።
በህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር እና ሌሎች ተያያዥ ህገ-ወጥ እንቅስቃሴዎች ላይ በተደረገው ቁጥጥር ከ55 ሺህ በላይ ግለሰቦች ላይ ህጋዊ እርምጃ መወሰዱን አስታውቀዋል።
እንዲሁም ተገቢነት ያለው ምዝገባ ያላደረጉ የነበሩ የተለያዩ ሀገራት ዜጎች ወደ ህጋዊ መስመር እንዲገቡ መደረጋቸውን አመላክተዋል።
የተቋሙን የሰው ኃይል አደረጃጀት እና ልማት በማሻሻል አገልግሎቱን ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ የተከናወኑ ተግባራት ለውጡን ለማረጋገጥ ወሳኝ እንደነበሩም ገልጸዋል።
የኤሌክትሮኒክ ፓስፖርት አገልግሎት ለሚፈልጉ በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በሚሲዮኖች አማካይነት ከፊታችን ሐምሌ 15 ጀምሮ አገልግሎቱን ማግኘት እንደሚችሉ ጠቁመዋል።
የተቋሙን አገልግሎት የሚፈልግ ማንኛውም ግለሰብ ከሚመለከታቸው ህጋዊ ተቋማት ብቻ ማስረጃዎችን ይዞ መቅረብ እንዳለበትም አሳስበዋል።