ቀጥታ፡

በክልሉ በበጀት ዓመቱ በገጠርና ከተማ ከ72 ኪሎ ሜትር በላይ የመንገድ መሠረተ ልማት ተገንብቷል 

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 9/2018(ኢዜአ)፦ በሀረሪ ክልል በ2018 በጀት ዓመት በገጠርና ከተማ ከ72 ኪሎ ሜትር በላይ የመንገድ መሠረተ ልማት መገንባቱን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ገለፁ።

ርዕሰ መስተዳድሩ ይህንን የገለፁት እየተካሄደ በሚገኘው የሐረሪ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር 5ኛ ዓመት 10ኛ መደበኛ ጉባዔው ላይ ለምክር ቤቱ ባቀረቡት ሪፖርት ነው።


 

በሪፖርታቸውም በክልሉ በመንገድ መሰረተ ልማት ደህንነትን፤ ፍትሃዊነትንና ተደራሽነትን ለማረጋገጥና የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎትን ለማሻሻል በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በተለይም በከተማና በገጠር አዳዲስ የመንገድ መሰረተ ልማት የመገንባትና ነባር የመንገድ መሰረተ ልማት የመጠገን ስራ ሲከናወን ቆይቷል ብለዋል።

የመንገድ መሰረተ ልማት ስራዎች ገጠርን ከከተማ እንዲሁም የገጠር ወረዳዎችን የሚያገናኙ መሆናቸውን ጠቁመው በዚህም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በክልሉ በገጠርና ከተማ ከ72 ኪሎ ሜትር በላይ የአስፋልትና የጠጠር መንገዶች መገንባታቸውን ነው የተናገሩት።

በተጨማሪም በከተማ ከ8 ነጥብ 6 ኪሎ ሜትር በላይ በተለያዩ አካባቢዎች የመንገድ ድሬኔጅ የመገንባትና የመጠገን ስራዎች በትኩረት መከናወናቸውን ርዕሰ መስተደድሩ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም