በክልሉ የልማት ዕድሎችን፣ የሰው ኃይልንና እውቀትን አቀናጅቶ በመምራት በየደረጃው ተጨባጭ ውጤት ማስመዝገብ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የልማት ዕድሎችን፣ የሰው ኃይልንና እውቀትን አቀናጅቶ በመምራት በየደረጃው ተጨባጭ ውጤት ማስመዝገብ ይገባል
አዳማ፤ሐምሌ 9 /2018 (ኢዜአ)፦በኦሮሚያ ክልል የልማት ዕድሎችን፣ የሰው ኃይልን እና እውቀትን አቀናጅቶ በመምራት በየደረጃው ተጨባጭ ውጤት ማስመዝገብ ይገባል ሲሉ የክልሉ ፕሬዚዳንት ሽመልስ አብዲሳ ገለጹ።
ላለፉት ሦስት ቀናት ሲካሄድ የቆየው የኦሮሚያ ክልል የ2018 በጀት ዓመት የመንግሥት እና የፓርቲ ሥራዎች ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ ተጠናቋል።
በመድረኩ ማጠቃለያ ላይ የሥራ አቅጣጫ የሰጡት የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ፣ ከመደመር እሳቤ የተቀዱ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች በፓርቲ፣ በመንግሥት መዋቅርና በተቀናጀ የሕዝብ ተሳትፎ እየተተገበሩ መሆኑን ተናግረዋል።
ይህም በ2018 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም ውስጥ በተጨባጭ የታየ መሆኑን ጠቅሰው፣ የተመዘገቡት ድሎች ቀጣይነት እንዲኖራቸው አመራሩ በላቀ ቁርጠኝነት መንቀሳቀስ አለበት ብለዋል።
የክልሉ አመራር በሁሉም መስክ ያሉትን የልማት ዕድሎች፣ የሰው ኃይልና ዕውቀትን አቀናጅቶ በመምራት የተጀመረውን የብልጽግና ጉዞ ማጠናከር እንዳለበት አስገንዝበዋል።
በተያዘው በጀት ዓመትም የተያዙ ግቦችን ለማሳካት ምቹ የልማት ዕድሎችን መጠቀም እንዲሁም የፋይናንስ አቅምና አማራጮችን ማስፋት ይገባል ብለዋል።
በአጠቃላይ የክልሉ አመራር በአዲሱ በጀት ዓመት የልማት ዕድሎችን በሚገባ የሚረዳ፣ ምርታማነትን ለማሳደግ አቅዶ የሚሠራ፣ ቁጠባና ኢንቨስትመንትን የሚያስፋፋ እንዲሁም የሕዝብ እና የአጋር አካላትን ሚና አቀናጅቶ መምራት እንዳለበትም አስረድተዋል።
በብልጽግና ፓርቲ የኦሮሚያ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ከፍያለው ተፈራ በበኩላቸው፤ የክልሉ አመራር የብልጽግና ጉዞ ግቦችን ለማሳካት የበለጠ መትጋት አለበት ብለዋል።
ያለፉት ዓመታት የብልጽግና ጉዞ በብዙ ፈተናዎች የተሞላ ቢሆንም፣ አመራሮቻችንና ፓርቲያችን ታሪክ ለመሥራት አልመው በመንቀሳቀሳቸው ፈተናዎችን ወደ መልካም አጋጣሚ መቀየር ተችሏል ሲሉም አክለዋል።
የተገኙ ድሎችን ለማስቀጠል በክልሉ ያለውን ሰፊ የልማት ዕድል እና የሰው ኃይል በቅንጅት በመምራት በሁሉም ረገድ ራስን ለመቻል በሚደረገው ጥረት የላቀ ስኬት ማስመዝገብ እንደሚገባም አሳስበዋል።