በዳኝነት ስርዓቱ የተካሄዱ የአሰራር ማሻሻያዎች ፈጣን፣ ግልጽና ተአማኒነት ያለው ፍትህ ለመስጠት አስችለዋል - ኢዜአ አማርኛ
በዳኝነት ስርዓቱ የተካሄዱ የአሰራር ማሻሻያዎች ፈጣን፣ ግልጽና ተአማኒነት ያለው ፍትህ ለመስጠት አስችለዋል
ባህር ዳር፤ሐምሌ 9 /2018 (ኢዜአ)፦ በዳኝነት ስርዓቱ የተካሄዱ የአሰራር ማሻሻያዎች ለህብረተሰቡ ፈጣን፣ ግልጽ እና ተአማኒነት ያለው ፍትህ መስጠት ያስቻሉ መሆናቸውን የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ አለምአንተ አግደው ገለጹ።
የክልሉ ፍርድ ቤት የ2018 በጀት ዓመትና የሶስት ዓመቱን የስትራቴጂክ እቅድ አፈጻጸም ግምገማ ዛሬ በባህር ዳር ከተማ አካሂዷል።
ፕሬዝዳንቱ አቶ አለምአንተ አግደው በመድረኩ ላይ እንደገለጹት ፣ የህግ የበላይነት መረጋገጥ ለክልሉ ሰላም፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እድገት መሰረት ነው።
በዚህም ባለፉት ሶስት ዓመታት የህግና ፍትህ ኢንስቲትዩትን እንደገና አደራጅቶ ወደ ስራ በማስገባት ዳኞችንና ሰራተኞችን በአመለካከት የማነጽ፣ በእወቀትና ክህሎት የመገንባት ስራ መሰራቱን ገልጸዋል።
የዳኝነት አገልግሎትን ተደራሽ በማድረግና ዲጂታል ቴክኖሎጂን ተግባራዊ በማድረግ እንግልትን በመቀነስ፣ ግልጽና ተጠያቂነት ያለው አሰራር ማስፈን የተቻለ መሆኑን ተናግረዋል።
ከመደበኛ ፍርድ ቤቶች በተጨማሪ የባህላዊ ፍርድ ቤቶችን በማቋቋም የፍትህ ስርዓቱን ተደራሽ በማድረግ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት የተከናወኑ ተግባራት የሚበረታቱ መሆናቸውን ገልፀዋል።
በአሁኑ ወቅትም በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ ከመጣው ንግድና ኢንቨስትመንት ጋር ተያይዞ የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን ለመፍታት በባህር ዳር ከተማ ዓለም አቀፍ የግልግል ዳኝነት ማዕከል ለማቋቋም እየተሰራ ነው ብለዋል።
በክልሉ ከወረዳ እስከ ክልል ባሉ ፍርድ ቤቶችና የፍትህ አካላት ኃላፊነታቸውን በመወጣት ላስመዘገቡት ከፍተኛ ስኬት ምስጋና አቅርበው የተመዘገቡ ስኬቶችን የማስቀጠል ተግባራት ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።
በጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የስትራቴጂክ ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ፍሬው ታደሰ በበኩላቸው፣ ባለፉት ሦስት ዓመታት የዲጂታል ፍትህ አገልግሎት አሰጣጥ በስፋት ተግባራዊ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።
በጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ፣ በአራት ምድብ ችሎቶች ፣ በ14 ከፍተኛና በ27 የፓይለት ወረዳ ፍርድ ቤቶች "የስማርት ፍርድ ቤት" በማዘጋጀት የዳኝነት አገልግሎት መስጠት መቻሉን ተናግረዋል።
በ2018 በጀት ዓመት ብቻ 16 ሺህ 606 መዛግብት በኢ-ፋይሊንግ ስርአት በመክፈት ሁለት ሺህ 564 ደንበኞችን በስማርት ችሎትና በቪዲዮ ኮንፈረንስ የፍትህ አገልግሎት ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን አስረድተዋል።
የዲጂታል አገልግሎቱም ተገልጋዮች ወደ ከፍተኛና ጠቅላይ ፍርድ ቤት በመመላለስ ከሚደርስባቸው እንግልት ከመታደግ በተጨማሪ ያወጡት የነበረውን ከ51 ሚሊዮን ብር በላይ ማዳን መቻሉን አስገንዝበዋል።
ዛሬ በባህርዳር ከተማ በተካሄደው መድረክ ላይም የሃይማኖት አባቶች፣ የተቋማት ኃላፊዎች፣ የአገር ሽማግሌዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።