የዴሞክራሲ ተቋማትን ገለልተኛና ጠንካራ ለማድረግ የተተገበሩ የህግ ማዕቀፎች የዴሞክራሲ ባህል እንዲጎለብት አስችለዋል - ኢዜአ አማርኛ
የዴሞክራሲ ተቋማትን ገለልተኛና ጠንካራ ለማድረግ የተተገበሩ የህግ ማዕቀፎች የዴሞክራሲ ባህል እንዲጎለብት አስችለዋል
ሀዋሳ፤ሐምሌ 9 /2018 (ኢዜአ)፦የዴሞክራሲ ተቋማትን ገለልተኛና ጠንካራ ለማድረግ የተተገበሩ የአሰራርና የህግ ማዕቀፎች የዴሞክራሲ ባህል እንዲጎለብት ማድረጋቸውን በሲዳማ ክልል የሚንቀሳቀሱ የሲቪክ ማህበራት ገለጹ፡፡
ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ የዴሞክራሲ ተቋማት ጠንካራ መሠረት ይዘው በገለልተኛነት እንዲሰሩ የተፈጠረው ምቹ ሁኔታዎች ውጤት እያመጡ ናቸው፡፡
በጉዳዩ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው በሲዳማ ክልል የሚንቀሳቀሱ የሲቪክ ማህበራት እንደገለጹት፤ የሕግና የተቋማት ማሻሻያ አዳዲስ አዋጆች መጽደቃቸው ተቋማቱ ከፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ነጻ ሆነው እንዲንቀሳቀሱ አድርጓል።
ይህም የዴሞክራሲ ባህል እየተጠናከረ እንዲመጣ ትልቅ አስተዋጽኦ ማድረጉን ገልጸዋል።
የተቋማቱ መጠናከር የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥና አገልግሎት አሰጣጥን በማሻሻላል የሕዝብ አመኔታ እያደገ እንዲመጣ ማድረጉን ተናግረዋል።
ከማህበራቱ መካከል የኢየሩሳሌም የሕፃናትና ማህበረሰብ ልማት ድርጅት ሀዋሳና አካባቢው ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ሥራ አስኪያጅና የሲዳማ ክልል የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች አስተባባሪ አቶ ማስረሻ ክብረት፤ ተቋማቱ ገለልተኛ እንዲሆኑ መደረጉ ውጤት እያስገኘ ነው ብለዋል፡፡
በተለይ የሲቪክ ማህበራት በነፃነት እንዲሰሩ የተፈጠረላቸው ምቹ ሁኔታዎች በመጠቀም ዜጎች በልማት፣ በመልካም አስተዳደርና በምርጫ ያላቸው ተሳትፎ እንዲጎለብት ሲሰሩ መቆየታቸውን ገልፀዋል፡፡
ድርጅቱም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለሲቪክ ማህበራት በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ገለልተኛ ሆነው መታዘብ እንዲችል ያገኘውን ፈቃድ ተጠቅሞ ሃላፊነቱን መወጣቱን ተናግረዋል፡፡
ምርጫው ነጻ፣ አሳታፊና ተአማኒ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የመራጮችን ግንዛቤ ማሳደግ ላይ አበክሮ መስራቱንም አስታውሰዋል።
የሪሰረክሽን ኤንድ ላይፍ ዴቨሎፕመንት ኦርጋናይዜሽን የፕሮግራም አስተባባሪ አቶ ብስራት ቦርሳሞ በበኩላቸው፤ በሀገሪቱ ለውጡን ተከትሎ የዴሞክራሲ ተቋማት በተሻለ መንገድ እየተገነቡና አቅማቸው እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡
ተቋማቸውም ገለልተኛ ሆኖ በምርጫው ሂደትና በዴሞክራሲያዊ ሥርዐት ግንባታ ላይ እንዲሳተፍ ያገኘውን ዕድል በመጠቀም የበኩሉን ሚና እየተጫወተ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የምርጫ ቦርድ ከሲቪክ ማህበራት ጋር በቅንጅት ባከናወነው ተግባር በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የመራጮችን ግንዛቤ ማጎልበት ላይ በመስራት የዴሞክራሲ ባህል እንዲጎለበት አስተዋጽኦ ማድርጋቸውንም ገልጸዋል።
ለዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ሂደት የጠንካራ ተቋማት መኖር ወሳኝ መሆኑን የገለጹት አቶ ብስራት፣ የተጀመረው ተግባር መጠናከር እንዳለበትም ገልጸዋል፡